የሚዲያ ዘርፍ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና የብሔራዊ ልማት ምሰሶ በመሆኑ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

You are currently viewing የሚዲያ ዘርፍ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና የብሔራዊ ልማት ምሰሶ በመሆኑ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

AMN ህዳር 26/2018

የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የጋራ አህጉር ለጋራ አላማ በሚል መሪ ሃሳብ እንደገለጸዉ ታላቋ አፍሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪኳን በራሷ ብዕርና ድምፅ ለመጻፍ የገበየችበትን የፓን-አፍሪካ የሚዲያ ሽልማት (AMA) ለማስተናገድ የተመረጠችው አፍሪካዊት መዲናችን አዲስ አበባ፣ የላቀ ሃላፊነቷን በብቃት እየተወጣች ትገኛለች።

በመላ አፍሪካ ርዕሰ ከተሞች መካከል፣ ለዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲና የጋራ አህጉራዊ ተቋማት ማዕከል በሆነችው ምድራችን፣ ይህን ታላቅ የሚዲያ መድረክ ማስተናገድ ታላቅ ኩራት ነው።

የአፍሪካ ሕብረት መናኸሪያ፣ የዲፕሎማሲና የዓለም አቀፍ መድረኮች ማዕከል የሆነችው አዲስ አበባ፣ ለ2025 የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት መስተንግዶ የተመረጠችው በከንቱ አይደለም።

ከተማዋ በቅርብ ዓመታት ባሳየችው ፈጣንና የዘርፈ ብዙ ዘርፍን ባካተተ የለውጥ ጎዳና፣ ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር የሚወዳደር ዕድገት ማስመዝገቧ ለዚህ ምርጫ ዋነኛው ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌትና የፓን-አፍሪካኒዝም ታሪካዊ ምሶሶ መሆኗ፣ በታላላቆቹ የአፍሪካ የነጻነት አባቶች ልጆችና በአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ ትብብር የተዘጋጀውን የመጀመሪያ መርሐ-ግብር ለማስተናገድ ትክክለኛውን መሠረት ጥሏል።

አዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያከናወነችው የመሠረተ ልማትና የከተማ ገጽታ ለውጥ፣ ከተማዋን ለመላው አፍሪካ ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ሥራ አስፈፃሚዎች እና የፖለቲካ መሪዎች መደበኛና ምቹ መሰብሰቢያ አድርጓታል።

ከመላው አህጉሪቱ እና ከተለያዩ የዓለም አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎችን በምቾት የሚያስተናግደው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መገኛ መሆኗ፣ ለሽልማቱ እጩዎችና ለሚዲያ ባለሙያዎች መምረጥና መጓጓዝ ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርጓል።

ይህ ሽልማት ትክክለኛ የአፍሪካ ፍላጎት መገለጫ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው። ከ40 ሀገራት የተውጣጡ ከ800 በላይ የሚዲያ ባለሙያዎች በተለያዩ ዘርፎች የተሳተፉበት መሆኑ፣ ለአፍሪካ ሚዲያ ያለውን ዓለም አቀፍ ዕውቅናና ተስፋ ያሳያል።

ሚዲያ የኅብረተሰብን ዕድገትና ውድቀት የሚወስን ቁልፍ ኃይል ነው። ከውጪ የሚመጡ አሉታዊ ትርክቶችንና የአፍሪካን ደማቅ ማንነት የማያሳዩ ዘገባዎችን ለመቀልበስ፣ አፍሪካውያን ስለራሳቸው ማንነትና ስኬቶች በራሳቸው አንደበት መናገር አለባቸው።

የአፍሪካ ሚዲያ ሽልማት በጋዜጠኝነት፣ በብሮድካስቲንግ፣ በዲጂታል ሚዲያ እና በትርክት ግንባታ የአፍሪካ ስኬቶችን የሚያሳዩ የሚዲያ ተወካዮች በአንድነት የሚሳተፉበትና የሚሸለሙበት ታላቅ መድረክ ነው።

የዚህ ሽልማት ዋነኛ ዓላማም፡-

አፍሪካውያን ስለማንነታቸውና ስለ አፍሪካ ሕዝቦች ደማቅ ማንነት በራሳቸው እንዲተርኩ የሚያስችላቸውን ዕድል መፍጠር ነው። በሚዲያ ዘርፍ የሚታየውን የፈጠራ ሥራና ጥራት በማወደስ፣ የሙያውን ደረጃ ከፍ ማድረግ። ከመላ አኅጉሩ የመጡ የሚዲያ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ፣ የጋራ ሙያዊ ዕውቀትንና ትብብርን ማጠናከር።

ለአዘጋጆቹና አጋሮቹ: የአፍሪካ ሕብረት ብሮድካስቲንግ፣ የፓትሪስ ሉሙምባ ፋውንዴሽን፣ የክዋሜ ንክሩማህ ፋውንዴሽን፣ የምዋሊሙ ኒዬሬሬ ፋውንዴሽን፣ የኬኔት ካውንዳ ሌጋሲ ፋውንዴሽን፣ የሲሱሉ ፋውንዴሽን ለማኅበራዊ ፍትህ እና የፒኤልኦ ሉሙምባ ፋውንዴሽን ይህንን የጋራ ራዕይ ወደ ተግባር በመለወጣቸው ታላቅ አክብሮት ይገባቸዋል።

አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ ሚናዋና ለዲፕሎማሲያዊ መስተንግዶዋ ያላትን ብቃት በማረጋገጥ፣ የአፍሪካን የላቀ ሚና የሚያጎሉ ሁነቶችን ከመደገፍ ወደኋላ አይልም። የሚዲያ ዘርፍ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና የብሔራዊ ልማት ምሰሶ መሆኑን በመገንዘብ፣ የመንግሥት ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል። አዲስ አበባ የሰላም፣ የትብብርና የፓን-አፍሪካኒዝም መዲና ናት – የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review