የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበብ ቢሮ አዘጋጅነት በክፍለ ከተሞች መካከል የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ጨዋታ ውድድር በሀገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ መካሄድ ጀምሯል።
የባህል ሙዚቃ መሣሪያ ውድድሩ “ኪን አዲስ የሙዚቃ እስትንፋስ” በሚል በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባህል ኪነጥበብ ቢሮ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሉባባ ጀማል ገልጸዋል።
ውድድሩ የባህል መሣሪያ ተጫዋቾች አቅም የደረሰበትን ደረጃ ለመፈተሽ እና የባህል ሙዚቃ መሣሪያን ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ለውድድሩ አሸናፊዎች የማበረታቻ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ከእህት ከተሞች ጋር በሚኖር የተለያየ የባህል ትውውቅ መድረክ ቀዳሚ ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተመላክቷል።
ከዚህ ባለፈም መሰል የውድድር መድረክ ሙያተኞችን ለማነቃቃት እና ተተኪዎችን ለማፍራት የጎላ ድርሻ እንዳለውም ወ/ሮ ሉባባ ጀማል ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው