ሕዝብና መንግስት ተቀራርበው መሥራት በመቻላቸው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል

You are currently viewing ሕዝብና መንግስት ተቀራርበው መሥራት በመቻላቸው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – ሕዳር 27/2018 ዓ.ም

በየካ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች “የጉባ ብስራቶች፣ የመደመር መንግስት ትሩፋቶች!” በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚንስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፥ የመከላከያ ሚንስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር)፣ የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ነዋሪዎቹን አወያይተዋል።

ውይይቱ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ያከናወናቸውን ዘርፈ ብዙ ልማታዊ ሥራዎች በመገምገም እና የሕብረተሰቡን ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማዳመጥ ለቀጣይ የፖሊሲ ግብዓትነት ለመጠቀም ያለመ መሆኑን አወያዮቹ ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ ሚንስትር ዓለሙ ስሜ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ በከፍተኛ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈች ቢሆንም አሁን ላይ ግን በስንዴ አብዮት ከራስ ተርፎ ወደ ውጪ መላክ ችላለች፡፡

ሀገሪቱ የቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እና የጉባ ብስራት የኡጋዴን የጋዝ ምርትን ለመጀመር መሠረት በመጣል ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች ከራሷ አልፋ ለአፍሪካውያን የይቻላል መንፈስን ማስረጽ ችላለች ብለዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት እንደሀገር ቀና እንድንል ያደረጉ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ሚንስትሩ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት፣ የከተማና የገጠር የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ስኬት ሕዝብ ከተናበበ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገር መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በሌላ በኩል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ የዉይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሥራና ክህሎት ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ከነዋሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ሚንስትር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት ጉባ ሀገሪቱን ወደ ብልጽግና ማሻገር የሚቻልባቸው ዘመን ተሻጋሪ ትልልቅ ብስራቶች የተሰሙበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

መንግስት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እንደ ሀገር የነበሩ ስብራቶችን መጠገን ቢችልም አሁንም ግን ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን በመረዳት ከማኅበረሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን በየደረጃዉ ለመፍታት መንግስት ተግቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍል ከተማ በነበረው ውይይት ላይ የተገኙት አቶ ጃንጥራር አባይ የከተማ አስተዳደሩ የቤት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት፣ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል፣ የኢንዱስትሪውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ በኩልም የነዋሪውን ሕይወት ለመቀየር ያለውን ቁርጠኛነት ማሳያ አድርገው ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review