የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባንኮች የደንበኞችን ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥ እና ሀሰተኛ መታወቂያን ለመለየት ይወስድባቸው የነበረውን ጊዜ እና ገንዘብ በእጅጉ መቀነስ መቻሉን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤጀንት እና መርቻንት ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ ብሌን ኃይለሚካኤል ተናገሩ፡፡
በባንኩ አሰራር መሰረት ለደንበኞች ትክክለኛ አገልግሎት ለመስጠት የመጀመሪያው ተግባር የሚቀርቡ መረጃዎችን ማጣራት እንደሆነ የገለጹት አቶ ብሌን፣ ይህ አሰራር ረጅም ጊዜ ይወስድ ነበር ብለዋል፡፡
አቶ ብሌን አክለውም መረጃው ተጣርቶ እስኪመጣ ድረስ ባንኩ ለደንበኞች አገልግሎት ለመስጥ ይቸገራል፤ ደንበኞችም መጉላላት ይደርስባቸዋል፡፡
አንዳንድ የሚቀርቡ ማስረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው እያለ በስህተት ክፍያ እንደሚፈፀምና በሂደት ሲጣራ ግን ሀሰተኛ ሆነው ሲገኙ ክፍያውን የፈፀሙ ባለሙያዎች ለአደጋ ይጋለጣሉ፤ ባንኩንም ለኪሳራ ይዳርጋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ግን የፋይዳ መታወቂያ በመምጣቱ የደንበኞችን ማንነት እና የሚቀረበውን መረጃ በቀላሉ ለመለየት ስለሚያስችል ጊዜን፣ ጉልበትንና ገንዘብን በመቀነስ በኩል ለባንኮች ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአስማረ መኮንን