ባህላዊ ስፖርቶችን ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ ለመውሰድ ምን ይሰራ?

You are currently viewing ባህላዊ ስፖርቶችን ወደ ዓለም አቀፉ መድረክ ለመውሰድ ምን ይሰራ?

የዓለም ቴኳንዶ ፌዴሬሽን መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ወደ 10 የሚደርሱ የቴኳንዶ ስፖርት ዓለም አቀፍ ውድድሮች ይካሄዳሉ፡፡ በእነዚህ ውድድሮች ላይ ታዲያ ባህላዊ ስፖርቱ ተጸንሶ ከተወለደበት ጃፓን በተጨማሪ በርካታ ሀገራት የአሸናፊነት ሜዳልያ የሚያጠልቁበት ጭምር ነው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት መካከል እንደ ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ፈረንሳይ፣ ብራዚል፣ ጀርመን፣ ቱርክዬና አዘርባጃን ያሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከአህጉረ አፍሪካም እንደ ግብጽ፣ ሞሮኮ እና አልጄሪያ የመሳሰሉ ሀገራት በስፖርቱ ውጤታማ ናቸው፡፡

በጃፓናውያኑ ተጠንስሶ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው የቴኳንዶ ስፖርት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደዚህ አይነት እውቅና ከማግኘቱ አስቀድሞ ግን ዓመታትን የፈጀ በርካታ ሂደቶችን ማለፍ ነበረበት፡፡ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1922 በጃፓን ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው ስልጠና በየትምህርት ቤቱ እንዲሰጥ ተደርጓል። ውድድሮች እንዲካሄዱ ደንቦችን በማዘጋጀት እ.ኤ.አ በ1957 በቶኪዮ የመጀመሪያውን የጃፓን ዩኒቨርሲቲ የካራቴ ውድድር አካሂደዋል። በ1964 እንደዚሁ የጃፓን ካራቴ ፌዴሬሽን መመስረቱን ተከትሎ በ1970 የዓለም ካራቴ ፌዴሬሽን ተቋቁሟል። እንዲ እንዲህ እያለ እ.ኤ.አ በ2016 ስፖርቱ በ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱም ጾታ እንዲካተት ተመርጧል።

ልክ እንደጃፓን ሁሉ የተለያዩ ሀገራት የራሳቸው የሆኑና ባህላቸውን፣ እሴቶቻቸውንና ማንነታቸውን የሚገልጡባቸው ባህላዊ ስፖርቶች አሏቸው፡፡ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያም ከታሪክና ከባህል ጋር የተቆራኙ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ክንውኖች አሏት። እነዚህ ስፖርቶች እንደ የፈረስ ጉግስ፣ የጦር ውርወራ፣ የገና ጨዋታ፣ ገበጣ እና ትግልን የመሳሰሉት የማንነት፣ ወግና ልማድ መገለጫዎች ናቸው።

በኢትዮጵያ የሚዘወተሩ ባህላዊ ጨዋታዎች በትክክል መቼ እንደተጀመሩ በጽሑፍ የተደገፈ መረጃ ባይገኝም ከክርስቶስ ልደት በፊት ይዘወተር እንደነበር በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡ በዚህም የክርስቶስ ልደት (የገና በዓልን) ምክንያት በማድረግ ከታህሣሥ ጀምሮ እስከ ጥር እና ከዚያም እስከ ክረምቱ መግቢያ ድረስ በብዛት ይጫወቱት እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያመላክታሉ፡፡

እነዚህ ባህላዊ ስፖርቶች ታዲያ ከስፖርታዊ ውድድርነት ባለፈ ትርጉማቸው ከፍ ያለና የታሪክና የባህል ማስረጃዎችም ጭምር ናቸው፡፡ የማኅበራዊ ትስስር ማዕከሎች ሆነውም ያገለግላሉ፤ እነዚህ ጨዋታዎች ሕዝብ ከሕዝብ የሚገናኝባቸው፣ ልምድ የሚለዋወጥባቸው እና የአንድነት ስሜት የሚጎለብትባቸው መድረኮች ናቸው፡፡

ይሁንና፣ እነዚህን ሀገራዊ ሀብቶች በዘመናዊ መንገድ አልምቶ፣ በሕግ ማዕቀፍ አስደግፎ እና ለዓለም አስተዋውቆ ለኢኮኖሚና ለዲፕሎማሲያዊ ጥቅም ለማዋል እየተሰሩ ያሉት ሥራዎችና የሚፈለገው ደረጃ ምን ይመስላል? የሚለው ጉዳይ ደግሞ ወሳኝ ይሆናል። ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ በኢትዮጵያ ከ294 በላይ ባህላዊ ስፖርቶች ያሉ ቢሆንም፣ ከዘመናዊ ስፖርቶች ጋር ሲነፃፀር ተገቢውን ትኩረት አላገኙም ማለት ይቻላል።

በ1977 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን የኢትዮጵያዊያን ልዩ መለያ የሆኑ ባህላዊ ስፖርቶች እና ጨዋታዎች በጥናት እና ምርመር በመታገዝ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይዘታቸውን ጠብቀው እንዲተላለፉ የማልማት፣ የማሳደግ፣ የመጠበቅ እና የማስተዋወቅ ስራዎችን በስፋት እየሠራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶች ፌዴሬሽን በጥናት አረጋግጨዋለሁ ባለው መረጃ መሰረት በመላው ኢትዮጵያ  ከ200 በላይ ባህላዊ የስፖርት ጨዋታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ባህላዊ ጨዋታዎች ታዲያ የተለያዩ አካባቢዎችና የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ማንነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ባህላዊ ስፖርቶች መካከል ደግሞ ህግና ደንብ ወጥቶላቸው በውድድር መልኩ እየተካሄዱ ያሉት አስራ አንዱ ብቻ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ዋነኛ ስራው ባህላዊ ስፖርቶችን ማስተዋወቅ፣ ማሳደግና ማበልጸግ ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ባህላዊ ስፖርቶችን ወደ አንድ መድረክ እያመጣ በውድድር መንፈስ እንዲዘወተሩ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ባህላዊ ስፖርቶች ከሀገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲተዋወቁ ብዙ መሰራት ያለበት ነገር አለ ይላሉ የባህላዊ ስፖርቶች ባለሙያው አቶ ይገረም ባየልኝ፡፡

በኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶች ፌዴሬሽን መረጃ መሰረት በየዓመቱ በሀገር አቀፍና በክልል ደረጃ ዓመታዊ የባህል ስፖርት ውድድሮች እየተካሄዱ ሲሆን፣ የባህል ስፖርቶች ይበልጥ እንዲዘወተሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ እንዲሁም የአሰልጣኝነትና የዳኝነት ሥልጠናዎች በፌዴሬሽኑ እየተሰጡ ነው። በየዓመቱ የሚደረጉት ውድድሮች ባህልና ወጉን ከማሳደጉም ባሻገር ለስፖርቶቹ ተተኪ ትውልድ ለማፍራት ዓላማ ይዘው የሚከወኑ ናቸው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን መረጃ ከሆነም ውድድሩ ወጥነት እንዲኖረውና ዘመናዊነቱን እንዲጠብቅ የተሰራው ትልቁ ነገር ወጥ በሆነ ህግ እንዲመራ መደረጉ ነው፡፡ የባህል ስፖርት ውድድሮች የነጥብ አያያዝ ወጥነት እንዲኖረውና ለዳኝነት እንዲመች ዳኞችን በማሰልጠን ህጎቹ እንዲታወቁ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም በየዓመቱ በፌስቲቫል መልክ በሚደረጉ ውድድሮች እስከ አንድ ሺህ የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ፡፡

በውድድር መልክ ካልሆነ ባህላዊ ስፖርቶችን ለማሳደግ አዳጋች ነው የሚሉት ባለሙያው አቶ ይገረም ባህላዊ ስፖርቶቹን ለማሳደግና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በፊስቲቫል መልክ ብቻ ሳይሆን ወጥነት ባለው መልኩ ዓመታዊ ውድድሮች መሰናዳት እንደሚኖርባቸው ይገልጻሉ፡፡

የዜጎችን የባህል ስፖርት ተሳትፎ ለማሳደግ እና ስፖርቱን ለማስፋፋት እንዲረዳ ታስቦ በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲ የወጣ ቢሆንም የሚጠበቅበትን ውጤት ማምጣት አልቻለም የሚለው ደግሞ የብዙዎች አስተያየት ነው፡፡

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ህይወት መሐመድ የባህል ስፖርቶችን በአፍሪካ ደረጃ ለማስተዋወቅ የአፍሪካ የባህል ስፖርቶች ኮንፌዴሬሽን ጋር ጠንካራ ግንኙነት ተፈጥሯል ያሉ ሲሆን፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በአዳጊዎች እና በትምህርት ቤቶች ስፖርታዊ ውድድር ላይ የባህል ስፖርት እንዱ የውድድር አካል ሆኖ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ይህም ለባህል ስፖርቶች ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ዩኒቨርስቲዎች የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ በጥናት፣ በምርምር እና በትምህርት እንዲሁም በስልጠና ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በቀጣይ የባህል ስፖርቶችን ለማሳድግ እና ለማስተዋወቅ የክልልና ከተማ አስተዳደር የባህል ስፖርት ፌዴሬሽኖችን ማጠናከር፤ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል ፕሮግራሞችን በማብዛት በስኬት ማጠናቀቅ፤ የ2026 የመጀመሪያውን የአፍሪካ ሀገራት የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫል በሀገራት ለማዘጋጀት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን መስራት እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡

እንደዚሁም የአርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ውድድር ማዘጋጀት፤ ለሁሉም ክፍት የሆነ የባህል ስፖርቶች ውድድር ማዘጋጀት፤ የውድድር ማቴሪያሎችን ስታንዳርድ ማዘጋጀት፤ ዘርፉን ለማዘመን እና ለማሳደግ ከፍተኛ የሆኑ የጥናት እና ምርምር ሰራዎችን መስራት እና ሌሎችም ስራዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ለዚህም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር እና በተቻለ ፍጥነት ወደስራ በመግባት አመርቂ ውጤት ማስመዝግብ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ሕይወት የባህል ስፖርቶች የማኅበረሰብ የፍልስፍና ውጤቶች ናቸው ያሉ ሲሆን፣ እንዲለሙ፣ እንዲተዋወቁ እና የቱሪዝም ግብዓት እንዲሆኑ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በካሪኩለም ተካትተው በትምህርት እንዲሰጡ ከፍተኛ ስራዎች እየተሠሩ ይገኛል ብለዋል። በተለይም ተተኪ ስፖርተኞችንና ባለሙያዎችን ማፍራት ከተቻለ ስፖርቱ ከውድድሩ ባለፈ የሀገሪቷን ባህል የሚያስተዋውቅና ለቱሪዝም እድገቱ አስተዋጽኦ የሚያበርክት በመሆኑ ትኩረት እንደሚያሻው እሙን ነው።

ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ባህላዊ ስፖርቶችን ወደ ዓለም መድረክ ለማውጣት እና ከጥፋት ለመታደግ የሕግ ማዕቀፍና ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ወሳኝ ናቸው። የባህል ስፖርቶች በብሔራዊ ሀብትነት እንዲታወቁና እንዲሁም ቅርጻቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ በሕግ መደገፍ አለባቸው። ለፈረስ ጉግስና ለጦር ውርወራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድሮችን ለማካሄድ እንዲቻል የቴክኒክ ሕጎች፣ የዳኝነት መስፈርቶችና የደህንነት ደረጃዎች በሕግ ማዕቀፍ ተቀርፀው መደራጀት አለባቸው። እንደዚሁም የስፖርቱን ልማት በዘላቂነት ለመደገፍ በጀት እንዲመደብና የፋይናንስ ምንጭ እንዲፈጠር ሕጋዊ መሠረት መጣል ያስፈልጋል።

ባህላዊ ስፖርቶቹ ‘የስፖርት ቱሪዝም’ (Sport Tourism) ተደርጎ ሊታይና በተመረጡ ታሪካዊ ቦታዎች በዓመታዊ ትዕይንትነት ሊቀርብ ይችላል። በሌላም በኩል ዓለም አቀፍ የስፖርት ሕጎች በማካተት ለምሳሌ የጦር ውርወራ (Javelin Throw) ዘመናዊ ቅርፅ እንዳለው ሁሉ የኢትዮጵያ ባህላዊ የጦር ውርወራም በልዩ የሕግ ማዕቀፍ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም።

የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀትና ማስፈጸም፣ የባህል ስፖርቶችን በብሔራዊ ሀብትነት የሚጠብቅ፣ የሚያለማና የማስተዋወቂያ ሥርዓት የሚያስቀምጥ ሕግ በአስቸኳይ ማውጣት እና የቱሪዝም ሚኒስቴርን፣ የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽንን እና የኢንቨስትመንት ተቋማትን በማቀናጀት ባህላዊ ስፖርቶችን ከቱሪዝም ፓኬጆች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም ባለሙያው አቶ ይገረም ያስረዳሉ። አክለውም ስፖርቶቹን በዘመናዊ መንገድ መመዝገብ፣ ዲጂታል ማኅደሮች ማዘጋጀት እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ማስተዋወቅ ይገባል ይላሉ።

የባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን አደረጃጀት በባለሙያ እንዲደግፍ ማድረግና ባለሀብቶች በፈረስ ጉግስና መሰል ስፖርቶች ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማበረታቻ መስጠትም ሌላኛው መፍትሔ ስለመሆኑ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡ ባህላዊ ስፖርት ከስሜት ተሻግሮ በሳይንሳዊ መንገድና በሕግ ማዕቀፍ ተደግፎ ከተሰራበት እንደ ጃፓን ‘ሱሞ’ ወይም እንደ ስፔን ‘ሮዲዮ’ የዓለምን ትኩረት መሳብ ብቻ ሳይሆን፣ በርካታ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቅሞች ማግኘት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ለአህጉር አቀፉ የአፍሪካ የባህል ስፖርቶች እና ጨዋታዎች ኮንፌዴሬሽን (African traditional sports and games confederation) ያቀረበው የአባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review