ኢትዮጵያ በስፋት እያከናወነች የምትገኘው የስንዴ ልማት ስራ ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ተግባር መሆኑን የናሚቢያ የግብርና ምክትል ሚኒስትር ሩት ማሳኬ ገለጹ።
የአፍሪካ ሀገራት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የጋራ ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አሳስበዋል። በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የመጣው የስንዴ ምርታማነት በአፍሪካ የግብርና ዘርፍ ስኬቶች መካከል አንዱ ነው።
ለበርካታ አስርት ዓመታት ኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎቷን ታሟላ የነበረው ከውጭ በምታስገባው ምርት ሲሆን ይህም ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከመዳረጉ ባሻገር የሀገር ውስጥ ፍላጎትን በበቂ ሁኔታ አይሸፍንም ነበር። በአጭር ጊዜ ውስጥ በስንዴ ራስን ከመቻል አልፋ ወደ ውጭ መላክ የተሸጋገረችው ኢትዮጵያ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት አስመዝግባለች።

የናሚቢያ የግብርና፣ የአሳ ሀብት፣ ውሃ እና የመሬት ሪፎርም ምክትል ሚኒስትር ሩት ማሳኬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያን እያደገ የመጣ የስንዴ ምርታማነት አድንቀዋል።
የኢትዮጵያ የስንዴ ምርታማነት ለአፍሪካ ምሳሌ የሚሆንና ሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ ሊወስዱበት እንደሚገባ አመልክተዋል። ናሚቢያ የበጋ የምስኖ ስንዴ ልማት ኢኒሼቲቮችን እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸው፥ ይህም ከኢትዮጵያ ስንዴ ልማት ሲደመር አፍሪካ በተቀናጁ ጥረቶች የምግብ ምርታማነትን ማሳደግ እንደምትችል የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ማሳኬ የአፍሪካ ሀገራት በግብርናው ዘርፍ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት በጋራ መስራት እንዳለባቸው አንስተዋል። ሀገራት የግብርና ፖሊሲዎቻቸውን ማሰናሰል፣ የቴክኒክ አጋርነት መፍጠር እና የጋራ ስምምነቶችን በማድረግ ግብርናውን ማሳደግ እና የጋራ እድገት ማስመዝገብ እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት።

በትምህርት እና በቴክኒክ አቅም ግንባታ መዋዕለ ንዋይን በማፍሰስ በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለውን የግብርና ንግድ ልውውጥን መጨመር እንደሚገባ ተናግረዋል። ምክትል ሚኒስትሯ ቀረጥን ጨምሮ በአፍሪካ ቀጣናዊ የንግድ እንቅስቃሴ እና የምግብ ተደራሽነትን የሚገድቡ አሰራሮችን ማስቀረት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም የግብርና ምርታማነት ስራዎችን በፋይናንስ መደገፍ አለባቸው ነው ያሉት። ባለሙያዎች ለአርሶ አደሮች በግ ብርና ስራዎች ላይ የእውቀት ልውውጥ መፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንዳለባቸውም ማሳሰባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።