የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ሁሉም አካባቢዎች እንደሚወዳደር አስታወቀ።
የኢዜማ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ኢዮብ መሳፍንት ፓርቲው ለ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እያደረገ ያለውን ዝግጅትን አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ ላይ እንዳሳወቁት ፓርቲው በምርጫው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሕዝብን ድምጽ ለማግኘት ላለፉት አራት ዓመታት ሲዘጋጅ ቆይቷል።
ኢዜማ በሰላማዊ መንገድ ብቻ መንግሥት ለመሆን እንደሚሠራ የገለጹት ደግሞ የፓርቲው ሊቀመንበር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር) ናቸው።
መንግሥት ምርጫውን ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚጠበቅበትን እንዲወጣና ባለድርሻ አካላትም ምርጫው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የድርሻቸው ኃላፊነት እንዲወጡ ኢዜማ ጥሪ አቅርቧል።
መራጩ ሕዝብም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ እና ሀሳብን መዝኖ እንዲመርጥ፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከስሜት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ ታቅበው የመፍትሔ ሀሳብ በማቅረብ ዕድሉን በኃላፊነት እንዲጠቀሙ ፓርቲው መልዕክት አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ምርጫውን ከፍ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ኢዜማ መጠየቁን ኢዜአ ዘግቧል።