ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእኛን ህይወት እንደታደጉት ሁሉ እኛም ከራስ አልፈን የሌሎችን ህይወት ለመታደግ በቅተናል ሲሉ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ሰልጣኞች ገለጹ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ የእኛን ህይወት እንደታደጉት ሁሉ እኛም ከራስ አልፈን የሌሎችን ህይወት ለመታደግ በቅተናል ሲሉ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ሰልጣኞች ገለጹ

AMN – ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም

በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት ተጋላጭ የሆኑ ሴትቶች፤ በለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና የክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በተፈጠረላቸው ዕድል በተለያዩ ዘርፎች ሰልጥነው አማራጭ የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማዕከሉ የስነ-ምግባር፤የስራ ባህል እና የስራ ስምሪት እንዲፈጠርላቸው የተገነባ ባለፈርጀ ብዙ ማዕከል መሆኑን በአንድ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡

ከንቲባዋ ልማት የሰውን ህይወት የማይቀይር እና ለሰው ተስፋ የማይሰጥ ከሆነ፤ ብቻውን መሰረት ልማት ሰርተን ሃገር ብሎም ከተማ ለውጠናል የሚል መለኪያ የሌለን በመሆኑ በብልፅግና ጉዞ መለኪያችን የሰውን ህይወት ከመቀየር ጋር የተቆራኘ ነው ማለታቸውም ይታወሳል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ይህን እውን ለማድረግ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ዙር በተለያየ የሙያ መስኮች ከማዕከሉ ሰልጥነው ለወጡት ተመራቂዎች የስራ እድል በመፍጠር ሁለተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ችሏል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በማዕከሉ በ4ኛው ዙር ከ1ሺ ያላነሱ ሴት ሰልጣኞች እየሰለጠኑ ይገኛሉ፡፡

በተለያዩ የሙያ መስኮች ሰልጥነው ወደ ስራ የተሰማሩ ሴት እህቶቻችን እንደተናገሩት በተፈጠረልን ልዩ እድል ከከባድና አስከፊ ከነበረው ህይወታችን ተላቀን ባገኘነው ልምድና በቀሰምነው እዉቀት የነገው ህይወታችን ብሩህ የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠር ችለናል ብለዋል፡፡

አክለውም በማዕከሉ በተፈጠረላቸው የስራ እድል መሰል ሴት እህቶቻቸውን እያሰለጠኑ እንደሚገኙ እና በከተማዋ ባሉ የመንግስት ተቋማት ሳይቀር እየተገኙ ስልጠና የሚሰጡ መኖራቸውንም ገልፀዋል፡፡

በወሰዱት ልዩ ልዩ የስራ ስምሪትም ለሌሎችም የስራ እድል በመፍጠር ህይወታቸውን ለመታደግ መብቃታቸውን ገልፀው፤ በዉጪ ሃገርም በተዘረጋው የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ይህም ሌሎች የእኛን ህይወት እንደታደጉት ሁሉ እኛም ከራስ አልፈን የሌሎችን ህይወት ለመታደግ የበቃንበት የከተማ አስተዳደሩ ፍሬ ማሳያ ነው ሲሉ መግለጻቸዉን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review