የኤርትራ መንግስት በቀይ ባህር የአፋር ሕዝቦች ላይ እያደረገ ያለውን የመብት ጥሰት ዓለም ሊያውቅ ይገባል ተባለ

You are currently viewing የኤርትራ መንግስት በቀይ ባህር የአፋር ሕዝቦች ላይ እያደረገ ያለውን የመብት ጥሰት ዓለም ሊያውቅ ይገባል ተባለ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ታኅሣሥ 15/ 2018 ዓ.ም

የኤርትራ መንግስት በቀይ ባህር የአፋር ሕዝቦች ላይ እያደረገ ያለውን የመብት ጥሰት ዓለም ሊያውቅ ይገባል ሲል የቀይባህር አፋር ዴሞከራሲያዊ ድርጅት ገለፀ።

ድርጅቱ ለብዙሀን መገናኛ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኤርትራ መንግሥት በደናከል አካባቢ በቀይ ባህር አፋር ሕዝቦች ላይ እየፈፀመ ያለውን መጠነ ሰፊ ፣ ስልታዊ ፣ መንግሥታዊ መር የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም የዘርማጥፋት ወንጀል ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን ገልጿል።

የቀይ ባህር የአፋር ሕዝቦች የሚደርስባቸው መከራን ለመከላከል ፣ የአለም አቀፍ ብዙሃን መገናኛ ድምፅ እንዲሆኑ እና አህጉራዊና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት ትኩረት እንዲሰጡ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥት ላይ ህጋዊ ፣ ዲፕሎማሲያዊ ፣ ሰብዓዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ እንዲወሰዱ እና ተፅዕኖ እንዲያሳድሩ መግለጫውን የሰጡ የድርጅቱ አመራሮች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኤርትራ መንግስት በአካባቢው ከህግ እና ከፍርድ ውጭ ግድያዎች እና ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ፣ ያለ ፍርድ ማሰር እና ማሰቃየት ፣ የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ ፣ በግዳጅ ማፈናቀል ፣ ፆታዊ ጥቃትን የአገዛዙ የአፈና መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ፣ ከሀገሪቱ ፖለቲካዊ አስተዳደር ማግለል ፣ የቀይ ባህር አፋር ሕዝብን ማንነትና ባህል ማጥፋት ፣ ኢኮኖሚያዊ መብቶቻችን መጣስ እና መሰል የመብት ጥሰቶች መፈፀማቸው ተጠቅሷል።

በዚህም ድርጅቱ ኤርትራ አባል የሆነችበትን የአፍሪካ ቻርተር የሕዝቦች መብት ኮንቬንሽን ላይ እውቅና ያገኙ 26 የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በመጣሱ ለአፍሪካ የሰብዓዊ እና ሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ሰኔ 04/2025 የክስ አቤቱታ 122 ገፅ ከሙሉ ማስረጃዎች ጋር አቅርቧል ብለዋል የድርጅቱ አመራሮች።

ይህ ሁሉ ሆኖም የኤርትራ መንግስት ከድርጊቱ ስላልተቆጠበ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ብዙሃን መገናኛ ትኩረት እንዲሰጡ በመግለጫው ተነስቷል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review