የአዲስ አበባ አዲሱ የስፖርት ወጋገን

You are currently viewing የአዲስ አበባ አዲሱ የስፖርት ወጋገን

ምቹ ባልሆኑና ደረጃቸውን ባልጠበቁ ሜዳዎች ስፖርታዊ እንቅስቀሴዎችን ማድረግ የአዲስ አበቤዎች ታሪክ አካል ሆኖ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋቾች የነበሩት እንደ ሳላዲን ሰይድ፣ አዳነ ግርማ፣ ሽመልስ በቀለና ጌታነህ ከበደን መሆን ህልማቸው የሆነ በርካታ አዳጊዎች አቧራ የለበሰ ፊታቸውን እየጠራረጉ የሸራ ኳስ የሚያንከባልሉባት እንደነበረች አይዘነጋም፡፡

በመዲናዋ ስመጥር የሆኑት እንደ አልማዝዬ ሜዳ፣ መላጣ ሜዳ፣ ብሪሞ እና ‘15 ሜዳ’ን የመሳሰሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች ደግሞ እነዚህ ህልሞች ይጻፉባቸው የነበሩ ገጾች ናቸው። በእርግጥ እነዚህ የስፖርት ሰፍራዎች የአዳጊዎቹን ህልም መሬት ለማውረድ ምቹ ስፍራዎች አልነበሩም፡፡ ለዓመታት አስታዋሽ አልነበራቸውምና አብዛኞቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የንጽህና ጉድለት ያለባቸው፣ ለአደጋ አጋላጭና አልፎ አልፎም ለአካባቢው ወጣቶች የሱስ ማስተናጋጃ ስፍራ ሆነውም አገልግለዋል።

አሁን ግን ሁኔታው እየተቀየረ ነው፤ ከፈረንሳይ ለጋሲዬን እስከ አልማዝዬ ሜዳ፣ ከሲኤምሲ እስከ ቤቴል ድረስ፣ ከብሪሞ እስከ ባንቢስ ስፖርታዊ ስፍራዎች አስታዋሽ አግኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ መረጃ እንደሚያመላክተው በከተማዋ ከ1 ሺህ 500 በላይ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደ አዲስ ተገንብተው ወደ አገልግሎት ገብተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ100 ያላነሱት በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት የተገነቡ ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የማህበራትና ውድድር ዳይሬክተር አያሌው ታደለ እንደሚገልጹት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለከተማዋ ድምቀት ከመሆን ባለፈ የህብረተሰቡን የስፖርት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እና የስፖርት ዓይነቶች ያካተቱ መሆናቸው ቀደም ሲል ከነበሩት የተለዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በተለይም የኮሪደር ልማቶች ላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተካትተው መሰራታቸው የቴኳንዶ ስፖርትን ጨምሮ ሌሎች ስፖርቶችን ለማስፋፋት እንደሚረዳም ታይቷል፡፡ የአዲስ አበባ የወርልድ ቴኳንዶ ፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ዋሲሁን የሚገለፁትም እየተሰሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ከተለመዱት እንደ እግር ኳስ፣ አትሌቲክስና መሰል ስፖርቶች ውጪ ላሉ የስፖርት አይነቶችም ዕድል የፈጠሩ ናቸው፡፡ በእርግጥም የስኬት ቦርድ ስፖርት ውድድር፣ የቴኳንዶ ፌስቲቫልና ትርዒትን የመሳሰሉ ስፖርታዊ ክንውኖች እየተለመዱ የመጡት ከአዳዲስ ስፖርታዊ ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋት ጋር ተያይዞ ነው፡፡

የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በርካታ መጫወቻ ሜዳዎች ተገንብተዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት ተጎሳቁለው የነበሩ ሜዳዎችም ዛሬ ላይ ዘመናዊ የሜዳ ንጣፍ ተሰርቶላቸው ለመርገጥ የሚያሳሱ ምቹ የመጫወቻ ስፍራ ሆነዋል፡፡ አብዛኞቹ እንደ አዲስ የተሰሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በምሽት ጨዋታ እንዲደረግ የሚያስችል መብራት ጭምር የተገጠመላቸው ናቸው። በበጋው ወቅት አቧራማ ክረምት ሲገባ ደግሞ ከመቅፅፈት የሚጨቀዩት ሜዳዎች ዛሬ ላይ መልካቸው ተቀይሯል። መጫወቻ ሜዳዎቹ ዛሬ ላይ ዘመናዊ የሜዳ ንጣፍ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መቀመጫዎችና አጥር ተሰርቶላቸው ምቹ ሆነዋል፡፡

ወጣት በረከት ሙሉነህ የሚለውም ይህንኑ ነው፡፡ ወጣቱ በረከት በሰጠን አስተያየት፣ “አሁን ላይ የቅርጫት ኳስና እግር ኳስ የምንጫወትባቸው ሜዳዎች ምቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ግን በአብዛኛው የምንጫወተው የመኪና መንገድ በመዝጋት በመሆኑ ብዙ ችግሮችን አሳልፈናል፡፡ ለከፍተኛ ጉዳትም እንዳረግ ነበር፡፡ ከተሽከርካሪ ጋር እየተጋፈጥን ጭምር ነበር የምንጫወተው” ብሏል፡፡

በአካባቢያቸው የነበረው ሜዳም ቢሆን ደረጃውን የጠበቅ ባለመሆኑ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ይጫወቱ እንደነበር የሚገልፀው ወጣት በረከት፣ አንዳንድ ጊዜም መጫወቻ ሜዳ ፍለጋ ከአካባቢያቸው ርቀው ለመሄድ ይገደዱ እንደነበርም ያስረዳል፡፡

ዮሴፍ አለባቸው አስተያየታቸውን ከሰጡን ወጣቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሁለት ወጣት ማዕከል ውስጥ በተሰራው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ውስጥ በሚገኝ ሜዳ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ያገኘነው፡፡ በግቢው ውስጥ እንደ አዲስ የተሰራው የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ እጅግ ዘመናዊና ለማንኛውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የተመቸ ስለመሆኑ ነግሮናል፡፡ ከዚህ በፊት ግን ሜዳው ደረጃውን የጠበቅ ባለመሆኑ ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው ይጫወቱ እንደነበር የሚገልፀው ወጣት ዮሴፍ፣ አንዳንድ ጊዜም መጫወቻ ሜዳ ፍለጋ ከአካባቢያቸው ርቀው ለመሄድ ይገደዱ እንደነበርም ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በከተማዋ ልዩ ቀለም ያለው ለሩጫ ብቻ ተብሎ በተዘጋጀው በርካታ ኪሎ ሜትሮችን በሚሸፍነው መንገድ ላይ የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ በርካታ የመዲናዋ ነዋሪዎች በየቀኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህም ማለዳ ተነስቶ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ ከአራት ኪሎ ቀበና መገናኛ፣ ከአራት ኪሎ ቦሌ አየር ማረፊያ፣ ከቦሌ ድልድይ መገናኛ፣ ከአዲስ ዓለም  አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እስከ ሲኤምሲ፣ በሌላ በኩልም ከሜክሲኮ አፍሪካ ህብረት፣ ሳርቤት፣ ወሎ ሰፈር አካባቢዎችን መመልከት በቂ ነው፡፡

ከፒያሳ፣ አራት ኪሎ፣ መገናኛና ቦሌን ይዞ ከተማዋን የሚያካልለው የኮሪደር ልማት ስራ ለስፖርቱ ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በስፖርት ወዳዱ የመዲናዋ ነዋሪ ዘንድ ምስጋና የተቸረውም ለዚሁ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ ነዋሪ የሆነው ዋለልኝ ተስፋዬ አስተያየትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ዘወትር እሁድ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የማድረግ ልምድ እንዳለው የሚገልጸው ወጣት ዋለልኝ ከዚህ ቀደም ንጹህና አረንጓዴ ከባቢዎችን በመዲናዋ ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበርና ለስፖርታዊ እንቅስቃሴም ምቹ እንዳልነበር ያስረዳል፡፡ እንደዚሁም የመዲናዋን ህዝብ የሚመጥን ሰፋፊ አረንጓዴ ስፍራዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ ስፖርት ልንሰራ ወጥተን በሽታ ሸምተን እንመለስ ነበር በማለት ያስታውሳል፡፡

የመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በአብዛኛው ተለውጠዋል በሚለው አሰተያየት የአዲስ ተስፋችን እግር ኳስ ፕሮጀክት መስራችና አሰልጣኝ መሐመድ ናስር ይስማማል፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የአዳጊና ወጣት ፕሮጀክቶች ስፖርቱን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ዋንኛ መሰረቶች ናቸው የሚለው አሰልጣኝ መሐመድ አሁን ላይ በመዲናዋ በሲኤምሲ አካባቢ ከ7 እስከ 17 ዓመት ያሉ አዳጊዎችን በፕሮጀክት አቅፎ በማሰልጠን ላይ ይገኛል፡፡

አሰልጣኙ እንዳለውም በመዲናዋ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እየተነቃቃና ተተኪ ተጫዋቾች እንዲፈጠሩ መሰረት እየጣለ ይገኛል፡፡ በተለይም ወጣቱ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በማጣቱ ምክንያት አልባሌ ቦታዎች ለመዋል ይገደድ እንደነበር አስታውሶ፣ አሁን ላይ ግን ንጽህና ያላቸውና ደረጃቸውን በጠበቁ መጫወቻ ሜዳዎች የመዲናዋ ወጣቶች በሚኖሩበት፣ በሚማሩበትና በሚሰሩበት አካባቢ በስፖርት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡

አሰልጣኝ መሐመድ አያይዞም እነዚህ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መሰራታቸው ይዞ የመጣው ብዙ ለውጥ እንዳለ ያስረዳል፡፡ አዳጊዎችን በፕሮጀክት ይዘው ለሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ደረጃውን በጠበቀ ስፍራ ማሰልጠን ስለጀመሩ፣ የስፖንሰር ድጋፍና ለስራቸው ተመጣጣኝ ክፍያ እንዲያገኙ አስችሏል። ለአዳጊዎች የሚሰጡ ስልጠናዎችም ሳይንሳዊና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና የጉዳት መጠን እንዲቀንስ እንዳገዛቸው አብራርቷል፡፡

እንደ አሰልጥኝ መሐመድ ማብራሪያ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው በማድረግ ከመንግስት ድጎማ ተላቅቀው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ይገባል። ተቋማቱ በባለሙያ እንዲተዳደሩ ቢደረግ፣ በአንዳንዶቹ ላይ ከመጫወቻ ሜዳ ውጪ እንደ መጻዳጃ ቤትና ፍሳሽ ማስወገጃ፣ ልብስ መቀያየሪያና መሰል ጉዳዮች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ አያይዞም የስፖርት ማዘውተሪ ስፍራዎቹ ተገቢው ባለሙያ ተመድቦላቸው እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባና ለምሳሌ መጫወቻ ሜዳዎቹ ውሃ የሚያጠጣ፣ ሜዳዎቹ እረፍት የሚያገኙበትን ጊዜ የሚቆጣጠርና ጥገና የሚደረግበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በበኩሉ፣ በከተማዋ የተገነቡ እና እየተገነቡ የሚገኙ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎች በህግ እንዲተዳደሩ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ በአዲስ መልክ የሚሰሩና ነባር የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገቢው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከማዕከል እስከ ወረዳ በቅንጅት መስራት እንደሚገባና የሁሉንም ማዘውተሪያዎች መረጃ በአንድ ቋት ማደራጀት የተጠያቂነት ስርዓት ለመዘርጋትና ይህም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎቹን በዘላቂነት ለመጠቀምና እየተነሱ ያሉ ችግሮችን በአስራር ለመመለስ ያስችላል ተብሏል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review