የኢትዮጵያ የዲጂታል 2030 ራዕይ በሀገሪቱ ለሚገኙ ዜጎች በሙሉ የ5ጂ የኔትዎርክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑን በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህንን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበትና የ“ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ እስከ 2030 ድረስ በሁሉም ሰነዶች ላይ ተፈጻሚ በሚሆንበት ሁኔታ ላይ በመከረው ፎረም ላይ ነው።
ህንድ ይህ ራዕይ ከግብ እንዲደርስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የተቀናጀ የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር ያለመውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ራዕይ በስፋት እየተገበረ መሆኑን አምባሳደር አኒል ኩማር ጠቁመዋል።
ይህም በፋይዳ መታወቂያ አማካኝነት “አንድ ሰው – አንድ ማንነት” እንዲኖር በማድረግ፣ ዜጎች የባንክና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያሰፉ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ የዲጂታል መታወቂያ እና የ5ጂ ቴክኖሎጂ ትስስር ዜጎችን ወደ ዘመናዊ የዲጂታል ባንክ ሥርዓት የሚያስገባ መሆኑ ተመላክቷል።
በዚህም ተጠቃሚዎች የባንክ አገልግሎትን በቀላሉ እንዲያገኙ፣ የብድር አቅርቦት እንዲመቻችላቸው እና ቁጥባቸውን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል።
በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው፣ የ5ጂ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ ሀገሪቱ ወደ አንድ የተቀናጀ የገበያ ሥርዓት እንድትሸጋገር ከማድረጉም ባለፈ፣ የእያንዳንዱን ግለሰብ ብቃት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በንቃት ለመጠቀም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።
በወርቅነህ አቢዮ