በድሮ አስተሳሰብ ባለመታጠር ፋይዳ ያለው የምርምር ሥራ መስራት ይገባል- ምሁራን

You are currently viewing በድሮ አስተሳሰብ ባለመታጠር ፋይዳ ያለው የምርምር ሥራ መስራት ይገባል- ምሁራን

AMN- ታኅሣሥ 28/2018 ዓ.ም

ምሁራን በድሮ አስተሳሰብ ሳይታጠሩ የዓለምን የቴክኖሎጂ ዕድገት ሂደት በመረዳት ለሕብረተሰቡ ቅርብ በመሆን ፋይዳ ያለው የምርምር ሥራ መስራት እንደሚገባ ምሁራን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ተገኝተው ከምሁራን ጋር ውይይት አድርገዋል።

“የምሁራን ሚና ለሀገር ብልጽግና” በሚል በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉ ምሁራንም መድረኩን አስመልክተው ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት እጅግ ጠቃሚ እንደነበርና የውይይት ባህል መዳበር እንደሚገባው ሀብታሙ ወንድሙ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡

ምሁራን “በድሮ አስተሳሰብ መታጠር” እንደማይገባቸው ያነሱት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ ምሁራን በያሉበት ዩኒቨርስቲ ራሳቸውን መፈተሸ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር የተነሳው ጉዳይም ጠቃሚነቱን በማንሳት፣ ዓለም የደረሰበት ለመድረስ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው፣ የውይይት መድረኩ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዩኒቨርስቲው የሰጡትን ትኩረት የሚያሳይ ነው ያሉ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረትም የዓለምን የቴክኖሎጂ ዕድገት ሂደት መረዳት ይገባል ብለዋል፡፡

ምሁራን ከውይይቱ በርካታ ቁምነገሮችን እንደወሰዱ የገለጹት ፕሮፌሰር የዓለምጸሃይ መኮንን፣ በውይይቱ የምሁራን የምርምር ሥራ ለሕብረተሰቡ ፋይዳ ያለው መሆን እንዳለበት መነሳቱ አግባብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕድገት የሚመጣው በምሁራንም፣ በመንግስትም እና በሕብረተሰብ ቅንጅት ነው ማለታቸው ያነሱት ፕሮፌሰር የዓለምጸሃይ፣ ይህንንም በመገንዘብ ሃላፊነትን መወጣት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው በትምህርት እና በቴክኖሎጂ መስክ ስለ ሀገሪቱ ያለፈ አሁናዊና ወደፊት የሚሆነውን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸው ተገቢ መሆኑን ያነሱት ደግሞ ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማሪያም ናቸው፡፡

ዓለም የደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ መፍጠንና መዘጋጀት እንደሚገባና ለዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸው የጎላ መሆኑን እንዳመላከቱ በማንሳትም፣ ምሁራንም ለሕብረተሰቡ ቅርብ መሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review