የበዓላት ሰሞን ባዛሮችን በማስፋት ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ በቅራቢያው የተረጋጋ ግብይት እንዲከውን ማድረግ ተችሏል

You are currently viewing የበዓላት ሰሞን ባዛሮችን በማስፋት ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ በቅራቢያው የተረጋጋ ግብይት እንዲከውን ማድረግ ተችሏል

AMN ጥር 3/2018 ዓ.ም

የበዓላት ሰሞን ባዛሮችን በማስፋት ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ በቅራቢያው የተረጋጋ ግብይትን እንዲከውን ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የገበያ ማረጋጋት ፤ የገቢ መሰብሰብ፤ ህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር እና የኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ ግብረ-ሀይል ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

ግብረ-ኃይሉ ባለፉት ሁለት ወራት የተሰሩ ስራዎችን ገምግሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የግብረ ሃይሉ ሰብሳቢ አቶ ጃንጥራር አባይ የተረጋጋና ጤናማ የግብይት ምህዳርን በመዲናዋ ለመፍጠር ደረጃቸውን የጠበቁ የገበያ ስፍራዎችን ከማስፋት ጀምሮ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ አምራቹን ከሸማቹ የማገናኘት ስራዎች በትኩረት መሰራታቸውን አንስተዋል።

በዚህም ገበያን የማረጋጋት ስራ ውጤታማ እንዲሆን አስችሏል።

በተለይ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ባዛሮችን በማስፋት ሁሉም የመዲናዋ ነዋሪ በአቅራቢያው የተረጋጋ ግብይትን እንዲከውን ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ጃንጥራር አባይ ይህም በዓልን አስታኮ ይፈጠሩ የነበሩ ያለተገቡ የዋጋ ጭማሪዎችን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል።

የህብረተሰቡን እርካታ በሚገባ ማረጋገጥ እንዲቻል አሁንም በርካታ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቃል ያሉት አቶ ጃንጥራር አባይ በተለይ ከዘይትና እንቁላል አቅርቦት ጋር ክፍተቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በቀጣይ በከተማ አስተዳደሩ በከተማ ግብርናና የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሮች የሚሰሩ ስራዎችን ከማጎልበት ባሻገር ከክልሎች ጋር በቅንጅት የአቅርቦት ምጣኔን የማሳደግ ስራ ቀዳሚው ትኩረት የሚደረግበት ነው ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከእንቁላልና ዘይት አቅርቦት ጋር ተያይዞ ለተነሱ ክፍተቶች የዶሮ መኖና የዘይት ማምረቻ ጥሬ እቃ እጥረት ምክንያት መሆኑን አስተው የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review