“ታላቁን ትረክት መቅረጽ ፤ አስፈላጊነቱን ማረጋገጥ እና ተቋማዊ ቅርጽ መፍጠር” ላይ ትኩረት ያደረገ ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በጅማ ከተማ እየተካሔደ ነው።
በሀገር አቀፍ ኮንፈረንሱ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚዲያና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች እንዲሁም ምሁራን ተሳትፈዋል።
አሰባሳቢ የወል ትርክት ለሀገረ መንግስት ግንባታ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሐመድ እድሪስ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ተናግረዋል።

“የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው” ያሉት ሚኒስትሩ የመደመር መንግስት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ የተለያዩ የአሠራር ስርዓቶችን ዘርግቷል ብለዋል።
አሰባሳቢ የወል ትርክት ለመገንባት በፖሊሲ የታገዘ ተቋማዊ ቅርጽ መፍጠር፣ በስርዓተ ትምህርት ማካተት፣ አሰባሳቢ የፖለቲካ ባሕል መገንባት እንደሚያስፈልግም ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
በኦሮሚያ ክልል አሰባሳቢና የወል ትርክት ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ናቸው።

የውይይት መድረኩን የስልጡንና ሰላማዊ ፖለቲካ ማዕከል (ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉል ፖለቲክስ) ከኦሮሚያ ክልል እና ጅማ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።
ለአሰባሳቢ የወል ትርክት ግንባታ ተቋማዊ ቅርጽ መስጠት፣ የአሰራር መርሆዎችን ማዘጋጀት እና የተቋማትን ኃላፊነቶች መበየን ከውይይቱ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው።
ካሳሁን አንዱዓለም