ልጆች፤ ጥምቀት በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በሀገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው። በዓሉ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ከጥር 10 ቀን ከተራ ጀምሮ በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ይከበራል፡፡ የኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት እንደየችሎታቸውና ማዕረጋቸው በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ተዘጋጅተው ነው ወደ አደባባይ የሚወጡት። ካህናት ታቦታቱን ከየመንበራቸው በማውጣት ወደተዘጋጀው ባህረ ጥምቀት ሲጓዙ፤ ወጣቶች በሆታና በዝማሬ እናቶች ደግሞ በእልልታና ጭብጨባ ጭብጨባ ማጀብ ያደምቃሉ።
የበዓሉ አከባበር ከዋናው የኃይማኖት መሰረታዊ ትርጉም ባሻገር በዓሉ ለሰው ልጆች ባህል፣ ኪነ ጥበብና ስነ ጥበብ ማደግ፣ በሕዝቦች መካከል ተፋቅሮና ተከባብሮ መኖር፣ ለገጽታ ግንባታነት እና ለቱሪስት መዳረሻነት ጠቀሜታው ብዙ ነው። ልጆች፤ ይህ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከልም አንዱ ነው፡፡
ታዲያ ልጆች ይህ የጥምቀት በዓል ከኃይማኖታዊ አከባበሩም ባለፈ ብዙ ትዕይንት የሚታይበት ነው፡፡ ታቦታት ከሚነሱበት እስከሚያድሩበት ስፍራ ድረስ ረጅም ጉዞ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ከጥምቀተ ባህሩ ጸበል ለመረጨት ሁሉም ይሽቀዳደማል፡፡ በዚህ ጊዜ ልጆች ከቤተሰቦቻችሁ ተለይታችሁ እንዳትጠፉና ሌሎች ተጨማሪ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በተመለከተ የአንድን አባት ምክር እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፡፡
አቶ አለማየሁ ተፈራ እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ነዋሪ ነኝ፡፡ ልጆች በቅድሚያ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ፡፡ የጥምቀት በዓል አይደለም እኛ ኢትዮጵያውያንን፤ የውጭ ሀገር ዜጎችም በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡
በዓሉ በከተማችን አዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች የሚከበር ሲሆን በጃንሜዳ በርካታ ታቦታት ያድራሉ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ማህሌትና ቅዳሴ ሲያደርጉ ካደሩ በኋላ ጠዋት ላይ ፓትርያሪኩ አሊያም ሊቀ ጳጳሱ ጥምቀተ ባህሩን ባርከው ወደ ህዝቡ በሚረጩበት ወቅት ትዕይንቱ ትልቅ ደስታን ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን ልጆች ጸበል ሲረጭ እናንተ ከቤተሰብ ተለይታችሁ ወደ ውስጥ መግባት የለባችሁም፡፡ የጸበል መረጨት ሥነ ስርዓቱ የድህነትና የምህረት በመሆኑ ታላላቆቻችሁን ባከበረ መልኩ ማድረግ አለባችሁ፡፡
ይህ የጥምቀት በዓል ሰው የሚበዛበት እንደመሆኑ መጠን በተለይም በእድሜ ትንንሽ የሆናችሁ ልጆች የእናትና አባቶቻችሁን እጅ በመያዝ ነው መንቀሳቀስ ያለባችሁ፡፡ ጥምቀተ ባህሩ አካባቢ ጸበል ለመረጨትም ሆነ ሌሎች መርሀ ግብሮችን ለመከታተል መሀል ውስጥ ገብታችሁ እንዳትጠፉ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባችኋል። ልጆች፤ ሁልጊዜ ጨዋታ ሊያታልላችሁ አይገባም። የቤተሰቦቻችሁንና የታላላቆቻችሁን ምክር መቀበልና መተግበር አለባችሁ፡፡ ከጓደኞቻችሁ ጋር የመጣችሁ ልጆችም ብትሆኑ በዓሉን ስታከብሩ ከጓደኞቻችሁ ተለይታችሁ እንዳትጠፉ እርስ በእርሳችሁ እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ መሆን አለበት፡፡
ልጆች ሌላው ጥንቃቄ ማድረግ ያለባችሁ ነገር መንገድ ላይ ያያችሁትን ነገር ሁሉ ግዙልን እያላችሁ ወላጆቻችሁን ማስጨነቅ፣ ራሳችሁንም ጤናችሁን ሊጎዱ የሚችሉ ምግቦችን ከመመገብ ልትቆጠቡ ይገባል፡፡
ብዙ የእግር ጉዞና እንቅስቃሴ ስለምታደርጉ ውሃ ሊጠማችሁ ይችላል። በዚህ ምክንያት ወላጆቻችሁን ያልተገባ ወጪ ከማስወጣት በምትኩ ከቤታችሁ በትምህርት ቤት ኮዳችሁ ወይንም በሌላ ለመያዝ በሚያመቻችሁ እቃ ይዛችሁ ብትወጡ ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጸሐይ እንዳይመታችሁ ኮፍያ ቢኖራችሁ ተመራጭ ነው፡፡
አዎ! ልጆች እንግዲህ በጥምቀት በዓል ገና ከቤት ወጥታችሁ ጥምቀቱን ወደ ማክበር ከመሄዳችሁ በፊት የወላጆቻችሁን ምክር ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ ከሄዳችሁም በኋላ ምክራቸውን መተግበር ላይ ልትዘናጉ እንደማይገባችሁ ከወዲሁ ልነግራችሁ እወድዳለሁ፡፡ ልጆች መልካም በዓል ይሁንላችሁ፡፡
በለይላ መሀመድ