በአፍሪካ ፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቃሴ ውስጥ ስመ ጥር ከሆኑት ታጋዮች አንዱ የነበረው ፓትሪስ ሉሙምባ ለሳምንታት ሲከናወን በቆየው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአካልም ባይሆን በመንፈስ በስታዲየም ታድሟል፡፡ የአፍሪካ የነፃነት ተጋድሎ ምልክት ብቻ ሳይሆን፣ በስፖርቱ ዓለም በተለይም በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ አሻራ ጥሎ ያለፈው መሪ በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ድግስ ላይ መነጋገሪያ ያደረገው ክስተት ተፈጥሯል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው በ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ስታዲየሞች በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ፣ አንድ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ደጋፊ ግን ለየት ባለ ሁኔታ ትኩረት ስቧል። ይህ ሰው ሚሼል ኩካ ምቦላዲንጋ ይባላል፤ ነገር ግን አሁን መላው አፍሪካ ‘ሉሙምባ ቬያ’ በሚል ቅጽል ስሙ ያውቀዋል። ደጋፊው ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቀኝ እጁን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ልክ በኪንሻሳ እንደሚገኘው የሉሙምባ ሃውልት በስታዲየም ያስመለከተበት ሁነት በብዙዎች ህሊና ውስጥ ተቀርፆ ቀርቷል። በሞሮኮ የተገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎችም ለአፍሪካ ኒውስ በሰጡት አስተያየት 35ተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ከሚሼል ኩካ ምቦላዲንጋን ውጪ ማስብ አንችልም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ይህንን ጨምሮ ያለፉት ቀናት በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሞሮኮ ሰማይ ስር፣ በአፍሪካ ዋንጫው ክራሞት አስደሳች፣ አነጋጋሪ እንደዚሁም በደስታና በሀዘን፣ በሽንፈትና ቁጭት መካከል የሚዋልሉ ታሪኮችን ሲሰንዱ ከርመዋል። የሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ መድረክ የጀመረው በ24 ቡድኖች አጀብ ቢሆንም፣ አሁን ግን መጋረጃው ሊዘጋ ጥቂት ሲቀረው መድረኩ ላይ የቀሩት ሁለት ‘ተዋናዮች’ ብቻ ናቸው። በዚህ ጽሑፍም 35ተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለየት ያሉ ክስተቶች ከብዙ በጥቂቱ አንዳስሳለን፡፡
ነገ መቋጫውን የሚያገኘው የአፍሪካ ዋንጫ፣ ገና ፍፃሜው ሳይደርስ በታሪክ ከፍተኛው የተመልካች ቁጥር የተመዘገበበት ውድድር በመሆን አዲስ ታሪክ ፅፏል። ውድድሩን ለማጠናቀቅ ሶስት ጨዋታዎች እየቀሩት፣ በወጣው መረጃ መሰረት 1 ሚሊዮን 116 ሺህ 950 ተመልካቾች በስታዲየም ተገኝተው ጨዋታዎቹን ታድመዋል። ይህም በአህጉሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛው የተመልካች ቁጥር ሆኖ ስለመመዝገቡ የካፍ መረጃ ያሳያል።
ለዚህ አስደናቂ ቁጥር መመዝገብ በዋናነት የሞሮኮ ዘመናዊ ስታዲየሞች እና በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የታገዙና ለተመልካች ምቹ የሆኑ መሠረተ ልማቶች ይጠቀሳሉ። እንደዚሁም ውድድሩ በዲጂታል አማራጮችና በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት በመላው ዓለም ከ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ሰዎች እየተከታተሉት የሚገኝ ሲሆን፣ ይህም የውድድሩን ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ከፍ ስለማድረጉ የኦሎምፒክስ ዶት ኮም መረጃ ያትታል።
ወደሌላኛው የውድድሩ አስገራሚ አጋጣሚ ስናመረ የምናገኘው የቡርኪና ፋሶው የመስመር ተጫዋች ጆርጂ ሚኖንጎን ይሆናል፡፡ በምድብ መጀመርያ ጨዋታዎች 12 ጨዋታዎች ተደርገዋል። በእነዚህ 12 ጨዋታዎች ታዲያ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ የነበረው የቡርኪና ፋሶው የመስመር ተጫዋች ጆርጂ ሚኖንጎ ነው፡፡ የ23 ዓመቱ ተጫዋች የተወለደው በኮትዲቯር ባቲብሊ ዶብሊ ይሁን እንጂ ለብሔራዊ ቡድን መጫወትን የመረጠው ግን ለቡርኪና ፋሶ ነው፡፡ እግር ኳሱን በተወለደባት ኮትዲቯር በልጅነቱ የጀመረው ጆርጂ ሚኖንጎ ከሁለት ዓመት በፊት በስፔን ልምምድ ላይ እያለ ድንገት በገጠመው የዐይን ህመም ብዙ ውጣ ውረዶችን አይቷል፡፡
በወቅቱ ወደ ጤና ተቋም ካመራ በኋላ የቀዶ ጥገና ህክምና ቢደረግለትም የገጠመው የዐይን ኢንፌክሽን ታክሞ የሚድን እንዳልሆነ እና ማየት የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይነገረዋል፡፡ በተጨማሪም የህክምና ባለሙያዎች ዳግም ወደ እግር ኳስ መመለስ እንደማይችልም አሳውቀውታል። ለእግር ኳስ የተለየ ፍቅር ያለው ጆርጂ ሚኖንጎ ምንም እንኳን አንድ ዐይኑን ቢያጣም መጫወትን ግን አላቆመም፡፡ ከቀደመው በተለየ መልኩ ልምምዱን አጠናክሮ በመቀጠል የተዋጣለት ተጫዋች መሆኑንም አስመሰከረ፡፡ በቼክ ሪፑብሊክ እና በአሜሪካ ሜጄር ሊግ ሶከር የመጫወት ዕድል ያገኘው ጆርጂ ሚኖንጎ በአፍሪካ ዋንጫ ቡርኪና ፋሶ ከመመራት ተነስታ ኢኳቶሪያል ጊኒን 2 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታ ሀገሩን ቀዳሚ ያደረገችውን ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል፡፡
የወቅቱ የሲያትል ሳውንደርስ የመስመር አጥቂ ስለሁኔታው ሲናገር “አይነስውር መሆኔ የተቃራኒ ቡድን ተከላካዮችን ለማየት ፈታኝ ቢሆንብኝም በሂደት ነገሮችን የመረዳት ዕድል አግኝቻለሁ” ብሏል፡፡ በሞሮኮ አፍሪካ ዋንጫ ገና ከጅምሩ ስሙን በደማቅ የጻፈው የ23 ዓመቱ ጆርጂ ሚኖንጎ ሌላ ታሪክ መስራትን ያልማል፡፡
ዶሚኒጌዝ ፔሌምቤ፣ ዴኒስ ኦንያጎ፣ ፒየር ኤምሪክ ኦባምያንግ፣ ኢድሪሳ ጋና ጊየ እና ብሩኖ ኢኩውሌ ማንጋ ዕድሜ ከቁጥርነት ያለፈ ትርጉም እንደሌለው ማሳያ የሆኑ አንጋፋ ተጫዋቾች ናቸው።
የ42 ዓመቱ ሞዛምቢካዊ አማካይ ዶሚኒጌዝ ፔሌምቤ የውድድሩ አንጋፋው ተጫዋች ነው። ሞዛምቢክ በኮትዲቯር 1 ለ 0 በተረታችበት የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ ዶሚኒጌዝ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ገብቶ ተጫውቷል። በሞዛምቢክ ማሊያ መጫወት ከጀመረ 22 ዓመታት ተቆጥረዋል። የቀድሞ የሱፐር ስፖርት ዩናይትድ፣ ማሚሎዲ ሰንዳውንስ እና ቢድቬስት ዊትስ አማካይ በዚህ ጊዜ ለሀገሩ ክለብ ዩዲ ሶንጎ እየተጫወተ ይገኛል።
የ40 ዓመቱ ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦንያንጎ በአፍሪካ ዋንጫው የተሳተፈ ሌላኛው አንጋፋ ተጫዋች ነው። ኦንያንጎ ከዚህ ቀደም ዩጋንዳን በ2017 እና በ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች በአምበልነት መርቷል። ከአራት ዓመት በፊት ጓንት መስቀሉን ይፋ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ውሳኔውን ቀልብሶ ዳግም ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተመልሷል።
ዴኒስ ኦንያንጎ በክለብ ደረጃ ለቅዱስ ጊዮርጊስና ማሚሎዲ ሰንዳውንስ ተጫውቷል። የ37 ዓመቱ ጋቦናዊ ተከላካይ ብሩኖ ኢኩሌ ማንጋ በአፍሪካ ዋንጫው የተጫወተ ሌላኛው አንጋፋ ተጫዋች ነው። ማንጋ ከአውሮፓውያኑ 2006 ጀምሮ በመድረኩ እየተጫወተ ይገኛል። ሞዛምቢካዊው ተከላካይ ሜክሰርም 37 ዓመት ሞልቶታል። ጋቦናዊው ፒየር ኤምሪክ ኦባምያንግ እና ሴኔጋላዊው ኢድሪሳ ጋና ጊየ ደግሞ 36 ዓመት ከደፈኑ በኋላ በአፍሪካ ዋንጫው የተጫወቱ ናቸው።
በአፍሪካ ዋንጫው በርካታ ተጫዋቾች በብቃታቸው ጎልተው የወጡ ሲሆን፣ ሞሮኳዊው የሪያል ማድሪድ ኮከብ ብራሂም ዲያዝ የውድድሩ ኮከብ እንደሚሆን ብዙዎች ግምታቸውን ከወዲሁ ሰጥተውታል፡፡ ዲያዝ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድንን ለመወከል በወሰነው ውሳኔ መሰረት ለመጀመሪያ ጊዜ በዋንጫው ላይ በመሳተፍ አስገራሚ ታሪክ እየሰራ ይገኛል። በ5 ጨዋታዎች ውስጥ 5 ጎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኖ እየመራ ነው። ዲያዝ በሜዳ ላይ ያለው ፍጥነትና የኳስ ቁጥጥር (Dribbling) ብቻ ሳይሆን፣ ወሳኝ በሆኑ ሰዓታት ጎል የመፍጠር ብቃቱ የሞሮኮን የማጥቃት መስመር እጅግ አስፈሪ አድርጎታል።
ናይጄሪያው አዴሞላ ሉክማን አንደዚሁ በውድድሩ የደመቀው ሌላኛው ኮከብ ሲሆን፣ ባለፈው የውድድር ዓመት በክለቡ አታላንታ ካሳየው ድንቅ ብቃት በኋላ፣ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም የናይጄሪያ የድል ቁልፍ ሆኖ ቀጥሏል። በምድብ ጨዋታዎች 4 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማመቻቸትና 3 ጎሎችን በማስቆጠር ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳርፏል። በምድብ ጨዋታዎች ማጠቃለያ ላይ በካፍ ምርጥ 11 ውስጥ የተካተተ ብቸኛው ናይጄሪያዊ ተጫዋች ሆኗል።
እስካሁን ባለው ሂደት 4 ጎሎችን ያስቆጠረው ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላህ፣ በተከላካይ መስመር ላይ ሆኖ በጨዋታ በአማካይ 3 ነጥብ 5 ግልጽ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ቀዳሚው የሆነው አሽራፍ ሀኪሚ እና ሳይቆጠሩባቸው የቀሩ ግቦችን (Expected Goals Prevented – xG Prevented) በተመለከተ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘው የደቡብ አፍሪካው ግብ ጠባቂ ሮንዌን ዊሊያምስም አስደናቂ ብቃታቸውን ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው እስካሁን ባለው ሂደት እጅግ አስገራሚ የሆኑ ቁጥራዊ መረጃዎችን እያስተናገደም ይገኛል። ውድድሩ የጎል ድግስ፣ ያልተጠበቁ ውጤቶችና አዳዲስ ታሪኮች የተመዘገቡበት ሆኗል። በአንድ ጨዋታ 2 ነጥብ 85 ጎሎች ሲመዘገቡ ይህ ውድድር ካለፉት 10 ዓመታት የውድድር ታሪክ ከፍተኛው የጎል አማካይ የተመዘገበበትና በምድብ ጨዋታዎች ብቻ ከ90 በላይ ጎሎች የተቆጠሩበት ስለመሆኑም የ‘ኦፕታ’ (Opta) መረጃ ያሳያል፡፡ አንደዚሁም በሞሮኮ እና ታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በተደረገው የምድብ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ በ18ኛው ሰከንድ ላይ የተቆጠረው ፈጣኑ ጎል በውድድሩ ታሪክ ካለፉት ፈጣን ጎሎች ተርታ የሚመደብ ሲሆን፣ ይህም ደጋፊው ገና ወንበሩ ላይ ሳይደላደል ስታዲየሙን ያስገረመ ክስተት ሆኖ አልፏል።
‘ኦፕታ’ን (Opta) ዋቢ አድርገን ስንቀጥል ሌሎች አስገራሚ መረጃዎችን እናገኛለን። በዚሁ መሰረት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን፣ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ያለው ስህተት ካለፈው ውድድር በ15 በመቶ ቀንሷል። የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን አማካይ አማዱ ኮናቴ 17 ዓመት በውድድሩ ላይ የተሳተፈው ትንሹ ተጫዋች ሲሆን፣ ይህ ወጣት በውድድሩ ላይ ጎል በማስቆጠርም አዲስ ታሪክ ጽፏል። ከፍተኛ ጎል አግቢው ብራሂም ዲያዝ በምድብ ጨዋታዎች ብቻ ያስቆጠራቸው የጎል ብዛት 5 ሲሆን፣ ይህም የወርቅ ጫማውን ፉክክር እጅግ አጓጊ አድርጎታል።
በአጠቃላይ፣ በሞሮኮ ምድር የተስተናገደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከእግር ኳስ ውድድርነቱ ባሻገር፣ አህጉሪቱ ያላትን የስፖርት መሰረተ ልማት ግንባታ ብስለትና የተጫዋቾቿን ታክቲካዊ እድገት ለዓለም ያስመሰከረበት ታላቅ መድረክ ሆኖ ተጠናቋል። የሞሮኮው ድግስ በነገው ዕለት ፍጻሜውን ቢያገኝም፣ በስታዲየሞቹ የታየው ስሜትና በኦፕታ መረጃዎች የተመዘገበው የታሪክ አሻራ ግን በአፍሪካ የእግር ኳስ ማህደር ውስጥ ለረጅም ጊዜ ሲታወስ ይኖራል። አሁን ጥያቄው በውድድሩ የታየውን ይህን የላቀ ደረጃ በቀጣይ ውድድሮች እንዴት ማስቀጠል ይገባል? የሚለው ሆኗል።