AMN- ጥር 22/2018 ዓ.ም
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ የንግድ ምክር ቤት የ2026 የዓመቱ “የኢንዱስትሪ ኢነርጂ ፕሮጀክት” (Industrial Energy Project of the Year) ተብሎ ተመርጧል።
የዕውቅና ሥነ-ሥርዓቱ ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ማታ በጋና አክራ፣ በኬምፐንስኪ ጎልድ ኮስት ሆቴል ተካሂዷል።
ዕውቅናው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለአፍሪካ አህጉራዊ ልማት ያለውን ታላቅ አስተዋጽኦ ለማረጋገጥ የተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
የዕውቅና ሽልማቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በመወከል በጋና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተጠባባቂ የሚሲዮን መሪ የሆኑት አምባሳደር አሣየ ዓለማየሁ (ዶ/ር) ተቀብለዋል።
በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ የኢንዱስትሪ እና ተቋማት ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች እና ሌሎች ታዋቂ እንግዶች ተገኝተዋል።
የአፍሪካ የንግድ ሽልማት ዳይሬክተር መሀሙዱ ሃያቱ፣ ምክር ቤቱ ፕሮጀክቱን ለመሸለም የወሰነው ግድቡ ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሽግግር፣ ለቀጣናዊ የንግድና የኤሌክትሪክ ትስስር ያለውን ጉልህ አስተዋጽኦ በመመልከት ነው ብለዋል።

ግድቡ በኃይል ማመንጨት አቅምና ዋስትና፣ እንዲሁም በረጅም ጊዜ የኢንዱስትሪ ሽግግር ላይ የተደረገ ታላቅ ኢንቨስትመንት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለግብርና ማቀነባበሪያ እና ለኢንዱስትሪ የእሴት ሰንሰለቶች መሠረት መጣሉንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በላኩት መልዕክት፣ ሽልማቱ የአፍሪካ ሀገራት የወደፊት ዕጣ ፈንታ በራሳቸው ሀብትና ጥረት ለመገንባት ያላቸውን የጋራ ምኞት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ግዙፍ፣ ውስብስብ እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች በአፍሪካውያን ታስበው፣ ተገንብተው እና ተመርተው ለአህጉሩ የጋራ ብልፅግና ሊውሉ እንደሚችሉ የሚያሳይ ህያው ምስክር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ-መር የልማት ጎዳና የምታደርገውን ስልታዊ ሽግግር የሚያሳይ ግልፅ ምስክር እንደሆነም ገልጸዋል።
ግድቡ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካዎችን በማንቀሳቀስ፣ የዲጂታል ሽግግርን በማገዝ እና በምስራቅ አፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ የኃይል ትስስርን በማጠናከር እንደ አህጉራዊ የኃይል ማዕከል እያገለገለ መሆኑ ተጠቅሷል።
ዕውቅናው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት የ2063 አጀንዳ ስኬት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፣ አፍሪካ በራሷ ኃይል ኢንዱስትሪዎቿን ማንቀሳቀስ እንደምትችል ለዓለም ያበሰረ ታሪካዊ ክስተት እንደሆነ መመላከቱን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።