AMN- የካቲት 4/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ እና አርአያ በመሆን መዝለቋ ይታወቃል።
ይህ የነፃነት ተምሳሌትነቷ ደግሞ በተግባር የታየው አፍሪካውያን አንድነታቸውን እንዲመሰርቱ ባደረገችው ጉልህ አስተዋጽዖ ነው። በዚህ የታሪክ ሂደት ውስጥ ደግሞ ስሙ ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር አብሮ የሚነሳ አንድ አንጋፋ ተቋም አለ- ጊዮን ሆቴል።
በእ.ኤ.አ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት፣ ለታሪካዊው ጉባኤ የመጡትን የጋናውን መሪ ክዋሜ ንክሩማህን ጨምሮ 32 የአፍሪካ መሪዎችን በክብር ያስተናገደው ጊዮን ሆቴል ነበር።
በወቅቱ ሆቴሉ የአፍሪካ መሪዎች የፖለቲካ ምክክር የሚያደርጉበት ብቻ ሳይሆን፣ ከሥራ ድካም በኋላ በታሪካዊው ‘የፒያኖ ምሽት’ መርሐ-ግብር የሚዝናኑበት ልዩ ስፍራ ነበር። ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ የአፍሪካ መሪዎችን በጋበዙበት ወቅት ራሳቸውም በዚሁ ሆቴል ያርፉ ነበር።

በሆቴሉ የሚገኙት ክፍሎች በወቅቱ የነበረውን የንጉሳውያን ደረጃ የሚመጥን የውስጥ ዲዛይን የተላበሱ ናቸው። ለየት የሚያደርገው ደግሞ ክፍሎቹ ሳሎንና መኝታ ቤታቸው ሳይለያይ፣ በሻተር ለመክፈትና ለመዝጋት እንዲያስችል ተደርገው በልዩ ጥበብ የተሰሩ መሆናቸው ነው።
ዛሬም ድረስ በክፍሎቹ ውስጥ ከፍራሹ በስተቀር ያ የጥንቱ ማራኪ ዲዛይን እንደነበረ ይገኛል። በሆቴሉ ታሪክ ውስጥ ደማቅ ትዝታ ጥለው ከለፉ መሪዎች መካከል የኒጀር መሪ አንዱ ናቸው።
መሪው ቁመታቸው እጅግ ረጅም ከመሆኑ የተነሳ፣ በሆቴሉ ሲያርፉ መደበኛው አልጋ ስላልበቃቸው ሁለት አልጋ ተቀጥሎላቸው እንዳረፉ በታሪክ ይነገራል።
ጊዮን ሆቴል ዛሬም ያንን ጥንታዊነቱን የሚወክል ድባብ እንደያዘ ይገኛል። ግዮን ሆቴል ጥንታዊ የንጉሳውያን ምግቦችንና መጠጦችን ለደንበኞች በማቅረብ፣ የጥንቱን የታሪክ አሻራ ለትውልድ እያስተዋወቀ ይገኛል።
በአጠቃላይ ጊዮን ሆቴልን ማንሳት ማለት የአፍሪካን አንድነት ማውሳት ነው። አባቶቻችን ለነፃነትና ለአንድነት የተጓዙበትን መንገድ የምንመለከትበት ይህ ተቋም፣ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ህያው ምስክር ሆኖ ይኖራል።
በታምራት ቢሻው