AMN- የካቲት 15/2018 ዓ.ም
የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦችን የነፃነት ተስፋ ያነገሰና የነጮችን የበላይነት ትርክት የሰበረ ታላቅ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን የታሪክ ምሁራን ይገለጻሉ።
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪው ዳግማዊ ተስፋዬ (ዶ/ር) ድሉ የጦርነት ውጤት ብቻ ሳይሆን የፓን-አፍሪካኒዝም መሠረትና የኢትዮጵዊያን የጽኑ አንድነት ማሳያ ነው ብለዋል።
እንደ ዳግማዊ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ከአድዋ ጀግኖች የሚቀሰመው ቀዳሚው ትምህርት ጽኑ አንድነት ነው። በወቅቱ የነበሩት ኢትዮጵያውያን በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ሳይከፋፈሉ ለሀገር ሉዓላዊነት በአንድ ዓላማ መቆማቸው ለድል አብቅቷቸዋል። ዛሬም ትውልዱ ልዩነቶችን አቻችሎ ለጋራ ብሔራዊ ግብ መቆም እንዳለበት ምሁሩ አሳስበዋል።
ሌላው ትልቅ ትምህርት የማይበገር ሥነ-ልቦና እና ራስን መቻል ነው። አርበኞቻችን ዘመናዊ መሣሪያ ባይኖራቸውም፣ “ለሀገሬ እሞታለሁ” በሚል የላቀ የሞራል ስንቅና የውጭ እርዳታ ሳይጠብቁ በራሳቸው አቅም ተንቀሳቅሰው ድል ተቀዳጅተዋል። ይህ ደግሞ የዛሬው ትውልድ በድህነትና በተግዳሮቶች ሳይሸነፍ በራሱ ጥረትና ድካም ተራራን መናድ እንደሚችል ትልቅ ማሳያ መሆኑ የታሪክ ምሁሩ ገልጸዋል።

ዳግማዊ (ዶ/ር) አክለውም፣ ትውልዱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በኢኮኖሚ ነፃነት ላይ ማተኮር እንዳለበት መክረዋል። አባቶቻችን በጦር ሜዳ ያመጡትን ድል፣ የዛሬው ትውልድ ሀገሪቱን ከልመናና ከዕዳ ጥገኝነት በሚያላቅቅ “የኢኮኖሚ አድዋ” ሊደግመው እንደሚገባ አሳስበዋል። ሀገር በምግብ ራሷን ካልቻለች ክብሯ ሙሉ ሊሆን እንደማይችልም ተጠቁሟል።
የአድዋ ድል የታየበት የይቅርባይነትና የጥበብ ስልት ለዛሬው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ችግሮች መፍትሔ መሆኑንም ገልጸዋል። መሳፍንቱ የነበራቸውን ቂም ወደ ጎን በመተው ለሀገር ቅድሚያ መስጠታቸውና ድሉ በዲፕሎማሲና በብልሃት የታጀበ መሆኑ፣ ትውልዱ ለዘመኑ ችግሮች በስሜት ሳይሆን በዕውቀትና በስልታዊ መንገድ መፍትሔ እንዲፈልግ ያስተምራል።
በመጨረሻም፣ አድዋ “አልቻልንም” የሚለውን የሽንፈት መንፈስ የሰበረ ድል በመሆኑ፣ የአሁኑ ትውልድ ካለበት የድህነትና የክፍፍል ቀንበር ለመውጣት እንደ አድዋ አርበኞች በአንድነት መነሳት ይኖርበታል።
ድሉ ያለፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሕያው መመሪያ መሆኑን ዶክተር ዳግማዊ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በቶለሳ መብራቴ