AMN – የካቲት 17/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በሐገረ መንግሥትነት ታሪኳ ውስጥ ታላቅ የታሪክ እጥፋት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችልና የመጻኢ ዕድሏን ግስጋሴ የሚቀይር መሠረት በጉባ ተራሮች ላይ ጥላለች።
ጉባ ኢትዮጵያዊያን የ21ኛው ክፍለ ዘመን ታላቁን ጀብድ የፈጸሙበት ስፍራ ሆኗል። የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የመልማት ሕልም የሚያሳይ ሕያው መልክ ነው።
ይህ ታላቅ ሕልም እውን ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያዊያን ከገንዘብ መዋጮ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለውለታል። ታሪክ መሥራትን ከአባቶቹ የተማረው የአሁኑ ትውልድ፣ ለልጆቹ የሚያስረክበውን ማርሽ ቀያሪ ገድል በላቡና በደሙ ገንብቷል።
የዓድዋ ድል ለጭቁን ሕዝቦች ሁሉ የነጻነት ጮራን እንደፈነጠቀ ሁሉ፣ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ “አይችሉም” የሚለውን የተስፋ መቁረጥ ትርክት ሰብሮ የልማት ብርሃንን ገልጧል። ግድቡ ኢትዮጵያውያን በፈተናዎች ሳይበገሩ ለታላቁ ሕልማቸው በጋራ የመጽናት ጀብዱን የተረከቡበት የዓድዋ የኩራት ውላጅ ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ከፍጻሜ የደረሰው በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶችን በጽናት በማለፍ ነው፡፡
ለአብነትም የቀደመ ብልሹ አሠራርን የማረም የቤት ሥራ፤ በሀገር ውስጥ አፈንጋጭ የፖለቲካ ኃይሎች የተፈጠሩ ውጥረቶች፣ የውጭ ኃይሎች የማዋከብ ዲፕሎማሲያዊ ደባ፣ ኮቪድ-19 ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ለሺህ ዓመታት 6 ሺህ 700 ኪሎ ሜትሮችን ሲኳትን የኖረው ዓባይ፣ ከዚህ በኋላ የቤቱ ባይተዋር አይሆንም። 1 ሺህ 680 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ማረፊያ ተሰናድቶለታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራትና በገንዘብና በእውቀት የተገነባ ታላቅ ተዓምር ነው። በ14 ዓመታት የግንባታ ሂደት ውስጥ ሦስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቢፈራረቁም፣ ሂደቱ ግን ጠንካራውን በማጎልበትና ጎዶሎውን በመሙላት ከግብ ደርሷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህንን ሕልም ያለሙ፣ ያሰቡ፣ ያስጀመሩና የተሳተፉ ጀግኖችን እናደንቃለን” ሲሉ የሀገር ግንባታ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚረጋገጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። የሕዳሴው ግድብ የቅኝ ግዛት ትርክትን በኃይል ለመጫን የተደረገውን ጥረት በመስበር የዚህ ትውልድ ዳግማዊ ዓድዋ ሆኗል።
ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የሐብቶቿ ባለቤት መሆኗን የማይፈልጉ ኃይላት ደባ ባይቆምም፣ ጉዞዋን ሊያዘገዩት እንጂ ሊያስቆሟት እንደማይችሉ በተግባር ተረጋግጧል።
ከዚህ ስኬት በኋላ የተሰሩ ግድቦች ድንጋይ ብቻ ሆነው እንዳይቀሩ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ወሳኝ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ እንደ ግብፅ ያሉ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትም ወደ ቀልባቸው ተመልሰው ይህን ሥራ እንዲደግፉ ይጠበቃል።
በታደሰ ሽፈራው