የአዲስ አበባን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የሚቀይረው አዲሱ ተንቀሳቃሽ ማዕከል

You are currently viewing የአዲስ አበባን የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የሚቀይረው አዲሱ ተንቀሳቃሽ ማዕከል

AMN- የካቲት 20/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት አገልግሎቶችን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ፣ በአውቶቡስ ላይ የተደራጀ ተንቀሳቃሽ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ወደ ሥራ ሊያስገባ መሆኑን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት አስታውቋል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ አገልግሎቱ ከተጀመረ ጥቂት ወራት ቢሆኑትም እስከ አሁን ከ100 ሺህ በላይ ተገልጋዮችን ማስተናገድ ተችሏል።

አገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ በ13 ተቋማትና በ107 የአገልግሎት አይነቶች የተጀመረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት አይነቶቹ ወደ 140 ማደጋቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

ይህንን ተደራሽነት ይበልጥ ለማስፋትም በተንቀሳቃሽ ማዕከላት የሚሰጡ ከ60 በላይ የዲጂታል አገልግሎቶች ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል።

በእነዚህ ተንቀሳቃሽ ማዕከላት ውስጥ የሚሰጡ ዋና ዋና አገልግሎቶች መካከል የቀበሌ መታወቂያ እድሳትና የሲቪል ምዝገባ፣ የመንጃ ፍቃድና የቦሎ እድሳት፣ የንግድ ፍቃድና የገቢዎች አገልግሎት፣ እንዲሁም የኤሌክትሪክ ክፍያና የፋይዳ (ብሔራዊ መታወቂያ) ምዝገባ ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ቅዳሜና እሁድን ጨምሮ፣ በተመረጡና የሰው እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው እንደ መስቀል አደባባይ እና ሃያት አደባባይ ባሉ ቦታዎች ላይ ለህዝብ ክፍት ይሆናል።

አዲሱ አሰራር በተለይ አገልግሎቶችን በኢንተርኔት (ኦንላይን) ለማግኘት ለሚቸገሩ ወይም በአካል መገኘት ለሚኖርባቸው ዜጎች ትልቅ እፎይታን ይሰጣል።

በተጨማሪም ተገልጋዮች ረጅም ጊዜ ወስደው ወደ መንግስት ቢሮዎች ከመሄድ ይልቅ፣ በእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው በቅርባቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በአሁኑ ወቅት በቦሌ እና በዋናው መሥሪያ ቤት ብቻ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት፣ በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ ወደ ዘጠኝ ተጨማሪ ቅርንጫፎች ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አቶ ዮናስ አለማየሁ አክለው ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review