AMN- የካቲት 21/2018 ዓ.ም
የ28ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዛሬም ቀጥሎ አምስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
ማንችስተር ሲቲ ከመሪው አርሰናል ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት ነጥብ ለማጥበብ በኤላንድ ሮድ ሊድስ ዩናይትድን ይገጥማል።
አርሰናል ከሰሜን ለንደን ደርቢ ድሉ በፊት የጣላቸውን ነጥቦች ተከትሎ ዕድሉን በሚገባ የተጠቀመው ማንችስተር ሲቲ ይህን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል።
ሁሌም የውድድር ዓመቱ ማብቂያ ላይ የሚጠነክረው የፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን በሁሉም ውድድር ባከናወናቸው አምስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ነጥብ አልጣለም።
ጠንካራ ጉዞ ላይ የሚገኘው ሲቲ በቅርብ ዓመታት ሊድስ ዩናይትድ ላይ ያለው የበላይነት የገዘፈ ነው። በሊጉ አምስት የመጨረሻ ግንኙነታቸው ሲቲ ሁሉንም በአሸናፊነት አጠናቋል። በእነዚህ አምስት ጨዋታዎች ሲቲ 19 ግብ ሲያስመዘግብ ሊድስ አራት ግቦችን ብቻ አስቆጥሯል።
ዛሬ ምሽት 2:30 በሚጀምረው ጨዋታ በሲቲ በኩል ዠርሚ ዶኩ ወደ ስብስቡ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ሊድስ ዩናይትድ አጥቂው ኖህ ኦካፎርን በጉዳት አያሰልፍም።
በሌሎች ጨዋታዎች በቀጣይ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ እየተጋ የሚገኘው ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ከ ዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ይፋለማል።
የባለፈው ዓመት የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል በ45 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ዌስትሃም ዩናይትድ በአንፃሩ በ25 ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሚደረገው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው ፍሎሪያን ቨርትዝን በስብስቡ እንደማያካትቱ አርነ ስሎት ተናግረዋል። በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ኤቨርተን እንዲሁም በርንሌይ ከ ብሬንትፎርድ ይጫወታሉ።
ቀን 9:30 ላይ ቦርንማውዝ በቪታሊቲ ስታዲየም ሰንደርላንድን ያስተናግዳል።
በሸዋንግዛው ግርማ