የደላላ ጣልቃ ገብነትን ያስቀረው የኮተቤው የገበሬዎችና አምራቾች ገበያ ለሸማቾች እፎይታን ሰጥቷል

You are currently viewing የደላላ ጣልቃ ገብነትን ያስቀረው የኮተቤው የገበሬዎችና አምራቾች ገበያ ለሸማቾች እፎይታን ሰጥቷል

AMN- የካቲት 22/2018 ዓ.ም

መንግስት የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ገበያውን ለማረጋጋት ግዙፍ የገበያ ማዕከላትን በመገንባትና የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን በማስፋፋት ሰፊ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ይሁንና ይህ የገበያ ማረጋጋት ተግባር የመንግስት ብቻ ሳይሆን አቅም ያላቸው ግለሰቦችና ማህበራትም ሊረባረቡበት የሚገባ ተግባር መሆኑ ይታመናል።

ይህንን መርህ ተፈጻሚ ለማድረግ በ85 አባላት ተመስርቶ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ስራ የጀመረው የኮተቤ የገበሬዎች አምራቾች አትክልትና ፍራፍሬ የገበያ ማዕከል፣ ስራ በጀመረ በሁለት ሳምንታት ውስጥ አመርቂ ውጤት እያሳየ መሆኑን ኤ ኤም ኤን በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።

ማዕከሉ ምርቶችን በቀጥታ ከአምራች አርሶ አደሮች ተረክቦ ለሸማቾች በማቅረብ ላይ ይገኛል። ይህም በተለይ በምርት ዝውውር ውስጥ የሚታየውንና ለዋጋ ንረት መነሻ የሆነውን ህገ-ወጥ የደላላ ጣልቃ ገብነትን በማስቀረት ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው።

በገበያ ማዕከሉ የሚሸጡ ምርቶች ከሌላው የከተማ ገበያ ጋር ሲነጻጸሩ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ እንዳላቸው ሸማቾች ይናገራሉ። ለአብነትም በሌሎች ቦታዎች በውድ ዋጋ የሚሸጠው ቲማቲም በማዕከሉ በ18 ብር፣ ሽንኩርት ደግሞ በ25 ብር ለሸማቹ እየቀረበ ይገኛል።

ይህም በቲማቲም ላይ የ12 ብር፣ በሀባብ ላይ ደግሞ እስከ 20 ብር የሚደርስ ቅናሽ በማሳየት የሸማቾችን የኢኮኖሚ ጫና ማቃለል መቻሉን ተጠቃሚዎች ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።

ከዋጋ ቅናሹ በተጨማሪ ምርቶቹ በቀጥታ ከእርሻ ቦታ የሚመጡ በመሆናቸው ያላቸው ትኩስነትና ጥራት ሸማቾች ማዕከሉን በዋነኛነት እንዲመርጡት አድርጓቸዋል።

የኮተቤ የግብርና ምርት አቅራቢዎች መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዘነበ ሽዋታጠቅ በበኩላቸው፤ የማህበሩ ዋና ዓላማ በአምራቹና በሸማቹ መካከል ያለውን የተንዛዛ የንግድ ሰንሰለት መበጠስ መሆኑን አስረድተዋል።

ማንኛውም አርሶ አደር የማህበሩ አባል ባይሆንም እንኳ ምርቱን አምጥቶ በዚህ ማዕከል መሸጥ እንደሚችልና ይህም ለአምራቹም ሆነ ለሸማቹ የተሻለ ተጠቃሚነትን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review