AMN- የካቲት 23/2018 ዓ.ም
አርሰናል በፕሪምየር ሊጉ መሪ እንዲሆን ካስቻሉት መመዘኛዎች አንዱ የቆሙ ኳሶች ስኬቱ እንደሆነ በርካታ ማሳያዎች አሉ።
መድፈኞቹ ትናንት ምሽት በተከናወነው የለንደን ደርቢ ጨዋታ ቼልሲን 2ለ1 ሲያሸንፉ ግቦቹን ያገኙት ከማዕዘን ምት ነው። በዚህም በሊጉ ከማዕዘን ብቻ ያስቆጠሯቸውን ግቦች 16 አድርሰዋል።
በአጠቃላይ ደግሞ 21 ግቦችን ከቆሙ ኳሶች አግኝተዋል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በቆሙ ኳሶች አጠቃቀም የተካና እንዲሆን ትልቁን ድርሻ አሰልጣኙ ኒኮላስ ዮቨር ይወስዳል።
የ44 ዓመቱ የቆሙ ካሶች አሰልጣኝ የሚካኤል አርቴታን የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የተቀላቀለው በ2021 ሃምሌ ወር ላይ ነበር።
ከዚህ በኋላ የዚህ ፈረንሳዊ አሰልጣኝ ሚና ጎልቶ እየታየ መጥቷል። በተለይ ዘንድሮ አርሰናል ዋንጫ ካሸነፈ ተመስጋኝ ከሚሆኑ ግለሰቦች መካከል አንዱ መሆኑ አይቀርም።
አርሰናል የኒኮላስ ዮቨርን አበርክቶ በምስጋና ብቻ አያልፈውም። ዘአትሌቲክ እንደዘገበው ከቆሙ ኳሶች ግቦች በተቆጠሩ ቁጥር አሰልጣኙ የገንዘብ ጉርሻ አለው።
በማንችስተር ሲቲ ሁለት ዓመት የሰራው አሰልጣኙ ይህን ውል የተፈራረመው በ2025 እንደሆነ ዘገባው አክሏል።
ኒኮላስ ዮቨር በበርካታ ክለቦች መፈለጉ አርሰናል አዲስ ውል ለማስፈረም እንዲጣደፍ አድርጎታል።
በሸዋንግዛው ግርማ