ኤርትራን የማስገንጠልና የባህር በር የማሳጣት ታሪክን በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም እየሰሩ ያሉ ቅጥረኞች

You are currently viewing ኤርትራን የማስገንጠልና የባህር በር የማሳጣት ታሪክን በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም እየሰሩ ያሉ ቅጥረኞች

AMN- የካቲት 25/2018 ዓ.ም

የአድዋ ጀግኖች የሃገራቸዉን ሉአላዊነትና ነጻነት ለማስከበር የከፈሉት አኩሪ ድል በየዓመቱ ታስቦ የሚዉል ሲሆን፣ 130ኛዉ የዓድዋ ድል በዓልም ፒያሳ በሚገኘዉ የአድዋ ድል መታሰቢያ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ታስቦ ዉሏል፡፡

የአድዋ ጀግኖች የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል የሆነዉን የአድዋን ድል በደምና በአጥንታቸዉ ለመጻፍ ከፍተኛ መስዋእትነት መክፈላቸዉን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

የአድዋ ጀግኖች ያን ጊዜ ባህር አቋርጠዉ፤ ድንበር ተሸግረዉ ከመጡ ፋሺስቶች ጋር ብቻ ሳይሆን የሃገራቸዉን ክብር ለዉጭ ወራሪ አሳልፈዉ ለመሸጥ ከጠላት ጋር ካበሩ ጥቂት ወንድሞቻቸዉ ጋርም ፊትለፊት ተጋፍጠዋል፤ታግለዋል፡፡

የሃገርን ክብር ለጠላት አሳልፎ የሚሰጥ ማንኛዉም ግለሰብ ቅጥረኛ እና ባንዳ ነዉ በማለት ጭምር ድርጊቱን በአደባባይ ኮንነዋል፤ አዉግዘዋል፡፡

የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአድዋ ድል መታሰቢያ በተከበረዉ 130ኛዉ የአድዋ ድል በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የአድዋ ጀግኖች በወቅቱ ፋሺስቶችን ብቻ ሳይሆን ቅጥረኞችንና ባንዳዎችን ጭምር ታግለዉ ነጻ ማዉጣታቸዉን ተናግረዋል፡፡

ለኢትዮጵያዊያን ሁለተኛዉ ዓድዋ በሆነዉ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅትም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ከ15 ሺህ የሚበልጡ ታጣቂዎችን ከሃገር ዉጭ በማሰልጠን ልማቱን ለማደናቀፍ መረባረባቸዉን አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የህዳሴ ልጆች በተለያዩ ወቅቶች የገጠሟቸዉን ፈተናዎች በጽናት እና በአንድነት በማሸነፍ ግድቡን አጠናቀዉ አስመርቀዋል፤ ህዳሴም ኃይል በማመንጨት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት ከብሔር ጥያቄ በስተጀርባ ሆነዉ ድጎማ እየሰጡ፤ እያስታጠቁ እንድንገዳደልና እንድንዳከም ሲያደርጉ የነበሩ አካላትን ተባብረን ባንመክታቸዉ ኖሮ ኢትዮጵያን አሁን ባለችበት ቁማና አናገኛትም ነበር፤ ባንዳዎች ዛሬም ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጎን ተሰልፈዉ የአድዋን ልጆች እየወጉ ነዉ ብለዋል፡፡

እነዚህ አካላት በህዝብና በብሔር ስም የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም ዋና አላማቸዉ ግን ኤርትራን የማስገንጠልና የባህር በር የማሳጣት ታሪክን በኢትዮጵያ ላይ ለመድገም እየሰሩ ያሉ ቅጥረኞች ናቸዉ ብለዋል፡፡

የብሄር፤ የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነዉ፤ እነዚህ ጥያቄዎች እንዲመለሱ ግን የሃገር እና የሉአላዊነት ምሽግ የሆነዉን የሃገር መከላከያ ሰራዊት መዉጋትና ማፍረስ አያስፈልግም ብለዋል፡፡

ከባዕዳን ጠላት ጋር ተሰልፎ የገዛ ሀገሩን ሰራዊት የሚወጋ ታጠቂ ባንዳ እንጂ ታጋይ ሊሆን አይችልም ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናግረዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review