AMN – የካቲት 24/2018 ዓ.ም.
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ የትግርኛ ቋንቋ ክፍል ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ሕዝብ ከራያና ወልቃይት የተፈናቀለ ቢሆንም በፕሪቶሪያ ስምምነት ማግስት ግን አብዛኛው ተፈናቃይ በሚባል ደረጃ ወደ ቤቱ ተመልሷል ብለዋል።
ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ ቀጥሎ የይገባኛል ጥያቄ ካሉባቸው ቦታዎች የተፈናቀሉም ወደ ራያና ፀለምቲ ተመልሰዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቸነከረ ሀሳብ የሚያራምደው የህወሓት ቡድን ግን ተፈናቃዮችን ለፖለቲካ ጥቅም ሲል እንደማስያዣ በመጠቀም ወደ ወልቃይት ለመመለስ አልተቻለም ብለዋል።
የፕሪቶርያ ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዳይተገበር ትልቁ እንቅፋት የሆነው ቡድኑ አምኖበት ከፈረመው ስምምነት ላይ የሚመቸውን አንቀጽ ብቻ መርጦ በመውሰድ ሕገ መንግስቱን እየጣሰ መቆየቱን ገልጸዋል።
ይህም ዳግም ግጭት እንዲከሰት ምክንያት መሆኑን ኮንነዋል።
የፌደራል መንግስት ከፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በኋላ ተፈናቃዮችን መመለሱ በቡድኑ የተደናቀፈ ቢሆንም አሁንም ትልቁ ስራ እነዚህ ተፈናቃዮች መመለስ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት የሚመለከታቸው አካላት አሁንም ኃላፊነታቸው አውቀው በሙሉ ዕምነት ከሠሩ ሁሉንም ችግሮቻችንን በዚህ ማዕቀፍ መፍታት እንችላለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
በምሩፅ ተስፋይ