AMN – የካቲት 24/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በትግርኛ ቋንቋ በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው የትግራይ ህዝብ ዕረፍት፣ ሰላም እና ልማት ይፈልጋል በማለት አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
የትግራይ ሕዝብ ሠላምና ልማት ይገባዋል፤ ሠላምና ልማትም ይወዳል፥ ለሠላምና ለልማት ታግሏል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ጦርነትና ውድመት አይገባውም የሚል ጽኑ ዕምነት ነው ያለኝ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ይህ ደግሞ በአረጀ አስተሳሰብ ሊረጋገጥ አይችልም። ሥልጣን የሕዝብ በመሆኑ በተማሩ ወጣቶች መመራት አለበት።
በእርጅናቸው ጊዜ ጦርነት የሚቀሰቅሱትን መሪዎች ሕዝቡ ሥልጣን ይበቃችኋል፥ ለልጆቻችሁ አስረክቡ ሊላቸውና ሕዝባችንና ሀገራችን ሰላም ይገባዋል የሚለውን መግለጽ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
በሁሉም ክልሎች እየመጣ ያለው ልማትና ሠላም ለትግራይ ክልልም ይገባዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰላም ፈላጊና ከተማሩ ወጣቶች ጋር ተባብረን ለትግራይ ክልል ሠላምና ልማት እንሥራ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በያለው ጌታነህ