AMN – የካቲት 25/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በበርካታ መስኮች የተከናወኑ የልማት ሥራዎች ከመዲናዋ ርቀው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ኑሯቸውን ያደረጉ ዜጎች ላይ አግራሞትን እየፈጠረባቸው ይገኛል፡፡
መዲናዋ ለለዋሪዎቿ የተመቸች፣ ለጎብኚዎች ደግሞ የስበት ማዕከል ትሆን ዘንድ ከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በርካታ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
በዚህም በመዲናዋ እስካሁን የተከናወኑ የልማት ስራዎች አዲስ አበባን መልካም ስምና ገጽታ ካላቸው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ተርታ እንድትወዳደደር እያስቻሏት እንደሆነ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ ዲያስፖራዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኑሯቸውን በሰሜን አሜሪካ ያደረጉትና ከኢትዮጵያ ከወጡ 20 ዓመታት ገደማ እንደሆናቸው የሚናገሩት የምህንድስና ባለሙያው ምንተስኖት ታምሩ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰራው የልማት ስራ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የህፃናት ትምህርት ቤቶች ሲገነቡ ከህንፃው መቆም በስተቀር ለህፃናቱ መጫዎቻና መዝናኛ ቦታዎ ምንም ትኩረት እንደማይሰጥ በማስታወስም፣ አሁን ላይ የሚገነቡ ትምህርት ቤቶች በአካባቢያቸው የመዝናኛ እና የመጫዎች ቦታዎች ያሟሉ በመሆናቸው በእጅጉ እንደተደሰቱ ተናግረዋል፡፡
ሌላው ካዛንቺስ አካባቢ የለማውና የህፃናት መንደር ተብሎ የተሰየመውን አካባቢ ሲመለከቱ እጅግ መገረማቸውን በመግለፅ፣ የዚህ አይነት ነገር እርሳቸው በሚኖሩበት ሰሜን አሜሪካም አይተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የ24/7 የሥራ ባህል በእጅጉ እንዳስደሰታቸውና ሰራተኞችም ለስራ ያላቸው ተነሳሽነት መጨመሩንም አድንቀዋል፡፡
ከ23 ዓመታት በላይ በአውስትራሊያ እንደኖሩ እና በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ እንደመጡ የሚገልጹት ዲያስፖራ ካሌብ ለማ፣ አዲስ አበባ ከተማ በጣም አምራና ተውባ እንደቆየቻቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ እንዲህ አምራና ደምቃ ስላገኘኋት በጣም ደስተኛ ነኝ በማለትም የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ የነበረው መሠረተ ልማትም ሆነ የከተማ ገጽታ የዘመነ እንዳልነበር የሚናገሩት ካሌብ፣ አሁን ላይ ግን በአዲስ አበባ በተሰራው የኮሪደር ልማት አማካኝነት በርካታ ለውጦች መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
በምሽት ብዙም የማይወጣባት የነበረችው አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ግን በማታ ሲወጡ እጅግ ያስደስታል ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ የሚታዩት ቅርፃቅርፆች የሀገርን ባህልና ወግ መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ከየትኛውም ዓለም ልዩ እንደሚያደርገውም አንስተዋል፡፡
ከዚህ በፊት እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ አንዳንድ ዜጎች ወደ አፍሪካም ሆነ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ብዙም ፍላጎት አያሳዩም ነበር ያሉት አቶ ካሌብ፣ አሁን ግን አዲስ አበባን ለማየት ጉጉትና ፍላጎት እያደረባቸው መጥቷል ብለዋል፡፡
ይህ የሀሳብ ለውጥ የመጣው በመዲናዋ የተሰሩት የልማት ስራዎች እጅግ ሳቢና ጎብኚዎችንም ያማከሉ መሆናቸውን በማንሳትም፣ የልማት ሥራው በዚህ ከቀጠለ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካዋ ኒውዮርክ ትሆናለች በማለትም ገልጸዋል፡፡
በአስማረ መኮንን