የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችእና ቀጣዩ ምርጫ

You are currently viewing የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችእና ቀጣዩ ምርጫ

• ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት በሚችሉበት ልክ መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል

በመለሰ ተሰጋ

ምርጫ እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በዴሞክራሲ ልማት ውስጥ ከፍ ያለ ትስስር አላቸው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለዜጎች መሪዎቻቸውን የመምረጥ መብት ሲሰጥ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ደግሞ ይህ ሂደት ፍትሐዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ተጠያቂነት ያለው መሆኑን ያረጋግጣሉ።

የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ ዴሞክራሲን ያጠናክራል የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ መሐመድ በሽር፤ ጠንካራ የሲቪክ ማህበራት የመራጮችን ግንዛቤና ተሳትፎ ከፍ በማድረግ ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ከምርጫ በኋላ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዲታረሙ በመታገል ጭምር በአንድ ሀገር ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ አሳታፊና ሰላማዊ ምርጫ እንዲከናወን ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡

ሲቪክ ማህበረሰብ በምርጫዎች ውስጥ በርካታ ጠቃሚ ሚናዎችን ይጫወታሉ የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ለአብነትም ስለ ምርጫው ሂደት፣ ስለ ሰላማዊ ተሳትፎ አስፈላጊነትና ስለ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ግዴታዎች ለመራጮች መሠረታዊ ትምህርት በመስጠት፣ ምርጫው ተአማኒ፣ ፍትሐዊና ግልፅ እንዲሆን በምርጫ ጣቢያዎች ጭምር ክትትል በማድረግ፣ በሂደቱ የተጎዳ ካለ ለፍትሕና ርትዕ ይሟገታሉ፤ በምርጫ ሂደትና ተያያዥ ጉዳዮችም የሕግ ክፍተቶች ካሉ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ይሟገታሉ፤ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በምርጫው እኩል ተሳትፎ እንዲኖራቸው ከግንዛቤ ፈጠራ እስከ ሰላማዊ ትግል ያደርጋሉ፤ በምርጫ ሂደቱም ግጭቶች አሊያም አላስፈላጊ ነገሮች እንዳይፈጠሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ለሰላምና መረጋጋት ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

አቶ መሐመድ በሽር እንደሚሉት ዴሞክራሲ በሕጎች ብቻ የተገነባ አይደለም። በንቁ እና በተደራጁ ዜጎች ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም በሕግ የተቀመጡ መብትና ግዴታዎች እንዲጠበቁ የሲቪክ ማህበረሰብ ሚና ጉልህ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን እንደሚሉት፣ ማህበራቱ ለትርፍ ያልተቋቋሙ፣ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው እና የማህበረሰብ ውክልና ያላቸው ተቋማት ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ማህበራት በልማት፣ በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ፣ በሰላም እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የማህበረሰቡን መብትና ጥቅም ማስጠበቅን ታሳቢ ያደረገ ዓላማን አንግበው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

ይህንንም መሠረት በማድረግ ተቋማቱ እንደ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን፣ በተለይም የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ 1113/2011 የተሰጠውን የተሻለ መብትና እውቅና መሠረት በማድረግ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

በተለይም ቀደም ሲል ተከልክለው በነበሩ ዘርፎች ለአብነትም በዴሞክራሲ፣ በሰላም እና በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ ጭምር እየሠሩ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል፡፡ እንደ ሀገር እውቅና የተሰጣቸው 5 ሺህ 700 የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን በሕገ መንግሥቱ መሠረት በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ ነው፡፡ ይህም ሂደት ሀገርን የሚመራ መንግሥትን ለመወከል የተለያዩ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ውድድር የሚያደርጉበት ነው፡፡ በመሆኑም ምርጫ ዋና የዴሞክራሲ ማዕከል ነው የሚሉት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችም የፖለቲካ ውግንና የሌላቸው በመሆኑም ምርጫን አስመልክቶ የተለያዩ ተግባራትን ይከውናሉም ብለዋል፡፡

ለአብነትም ምርጫውን አስመልክቶ ለመራጮች ትምህርት በመስጠት፣ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ ተአማኒ፣ ገለልተኛና ሰላማዊ እንዲሆን ለማስቻል ምርጫውን በመታዘብ እና ከምርጫ በኋላ እስከ ሌላኛው ምርጫ ባለው ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚናን ይጫወታሉ፡፡

ምርጫ ዜጎች የሚመራቸውን መንግሥት የሚመርጡበት እና የመጨረሻው ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን የሚያሳዩበት ትልቅ አጋጣሚ ነው፡፡ በመሆኑም ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለማምጣት የሚረዳ በመሆኑ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዚህ ስኬት ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ ነው፤ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ማህበራቱ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ምርጫ ሰዎች በካርዳቸው ብቻ መንግሥታቸውን የሚመርጡበት በመሆኑ መራጩ ሕዝብ ሂደቱን በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይዘውት የመጡትን አማራጭ ሐሳብ በሚገባ እንዲያውቅ፣ መብቱን እንዲጠቀም እና ሰላማዊ እንዲሆን፣ ችግሮችም ሲፈጠሩ ለምርጫ ቦርድ በማቅረብ እንዲፈቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ይሠራሉ፡፡

የሲቪክ ማህበራቱ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ መሠረት በማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን መሠረታዊ ጉዳዮች ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አህመድ፣ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ መሠረት በማድረግ 180 የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ከምርጫ ቦርድ ፈቃድ አግኝተዋል፤ በቅርቡ 34 ድርጅቶች የመራጮች ትምህርት ለመስጠት የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል፤ በሁሉም የምርጫ ክልሎች ተሰማርተው በተቀመጠው መርሃ ግብር መሠረት ሥራዎቻቸውን ያከናውናሉም ብለዋል፡፡

እንደ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ ሁሴን ገለጻ፣ ቀደም ሲል የነበረው የበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 በወቅቱ ከነበረው መንግሥት እሳቤ የመነጨ ነው፡፡ ይሄውም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን ከአጋር ይልቅ በስጋት የሚያይ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በመንግሥት ወይም በፓርቲያቸው የሚታዩት እንደ ልማት አጋር ሳይሆን በስጋትነት እንደነበር አውስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የወጣው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ቀደም ሲል አሳሪ የነበረውን እና በሕግ የተደገፈውን ስጋት የቀረፈ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ማህበራቱ በአግባቡ የመደራጀት መብታቸው ተከብሯል፡፡ ለአንድ ሀገር መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በምሶሶነት የሚገለጹ ናቸው። በመሆኑም በዚህ አዋጅ ይህ አስተሳሰብ የተገለጸና የመንግሥትን መልካም ፍላጎት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በበጎ አድራጎት ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ውስጥ በዴሞክራሲ፣ በሰላም እንደዚሁም በመብት ጉዳዮች ላይ ለመሥራት አስቸጋሪና ድርጅቶቹ በጀት ማምጣት የሚችሉት ከውጭ 10 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ በዚህም 1 ሚሊዮን ከውጭ የሚያገኙ ከሆነ ከሀገር ውስጥ 9 ሚሊዮን መሰብሰብ ግዴታ አለባቸው፡፡

ይህም ከነበረው ሁኔታ አንጻር መሥራት እንደማይቻል ያሳያል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ግን በፈለጉት ዘርፍ መደራጀት የሚችሉ መሆኑን እና ግልፅ በሆነ ዓላማ አዋጁን መሠረት አድርገው ከተንቀሳቀሱ መቶ በመቶም በጀት ከውጭ ማምጣት ይችላሉ፡፡

ቀደም ሲል ከፋፋይ የነበረውም ፍረጃ ቀርቶ ሁሉም ድርጅቶች እኩል በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በመሆኑም አዋጁ የአስተሳሰብ ለውጥ ያለበትና የማህበራቱን እንቅስቃሴና አሠራር ወደ ለውጥ ምዕራፍ ያሸጋገረ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀጽ 85 ላይ የተመሠረተ እና ሁሉንም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚወክል ነው። በሀገር ሰላም፣ በዴሞክራሲ፣ በሰብዓዊ መብት፣ በምርጫ እና መሰል ዘርፎች የለማና የሠለጠነ ማህበረሰብ ለመፍጠር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡

ምርጫ የአንድ ቀን ትዕይንት ባለመሆኑ ጠንካራ ሀገርና መንግሥት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም ትብብር ማድረግ እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ለምርጫ ህብረት ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለማርያም፣ ህብረቱ በሦስት መንገድ ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አውስተው፣ የመጀመሪያው ከመራጮች ትምህርት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና ማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም የሚተላለፍ ትምህርት ነው ብለዋል፡፡

ሁለተኛው አባል ድርጅቶች የተለያዩ የመራጮች ትምህርትን እንዲያካሂዱ የሚያስችላቸውን የበጀት ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻል ነው፤ በዚህም 14 ድርጅቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመራጮች ትምህርትን እንዲያካሂዱ የሚያስችላቸውን የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የቻሉ ሲሆን፣ ወደ ሥራ እየተሰማሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ሦስተኛው ደግሞ “የእሷ ድምፅ” የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አለ፡፡ በዚህም የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሌላው በቅድመ ምርጫ ታዛቢዎችን ማሰማራት፣ በምርጫ ቀን የሚሰማሩ ተቀማጭና ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን መመደብ እና በድህረ ምርጫ የሚሳተፉ ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን ማሰማራት ነው፡፡ በዚህ ሂደትም በአጠቃላይ ህብረቱ 5 ሺህ ታዛቢዎችን ያሰማራል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቅድመ ምርጫ ሂደቱ ምን እንደሚመስል ለአብነትም የሲቪክ ምህዳሩ፣ የመራጮች ምዝገባ፣ የምረጡኝ ትምህርት መስጠትን የመሳሰሉትን የሚታዘቡ 590 ታዛቢዎች ሥልጠና ወስደው በመሰማራት ላይ ናቸው፡፡

ሌላው የመገናኛ ብዙኃን ክትትል ሲሆን፣ ለዚህም የሚዲያ ሞኒተሪንግ ክፍል ተቋቁሟል፡፡ በዚህ ክፍል አማካኝነት በመንግሥትም በግልም ሚዲያዎች የሚደረጉ ክርክሮች፣ የአየር ሰዓት ሽፋኖች እና ተያያዥ ጉዳዮች ክትትል እየተደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ለምርጫ ህብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ እና አቅም ልክ የምርጫውን ሂደት ለመከታተል የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁንም በሚሠሯቸው ተግባራት ያጋጠማቸው ችግር አለመኖሩንም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አበራ ኃይለማርያም ተናግረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review