አዲሱ የህይወት ምዕራፍ

You are currently viewing አዲሱ የህይወት ምዕራፍ

• ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በአራት ዙር 2 ሺህ 401 ሴቶችን አስመርቋል

  • የ5ኛ ዙር ሰልጣኞችን ለመቀበልም በዝግጅት ላይ ይገኛል

ቤተልሄም ንጋቱ (ለዚህ ፅሁፍ ስሟ የተቀየረ) በሃያዎቹ አጋማሽ እድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ነች፡፡ ቤተሰቧን በሞት ማጣቷ እንዲሁም በኑሮ አጋጣሚ ለዓመታት መራራቋ ሕይወትን በብቸኝነት እንድታሳልፍ አድርጓታል። ቢያንስ የጠፉትን ማግኘት እንዳለባት ለራሷ በመንገር  ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ ሆኖም ያሰበችውን መፍትሔ ሊያስገኝላት አልቻለም፡፡

ይህች ወጣት ብቸኝነት ትከሻዋን ቢያጎብጠው “ምን አልባት ጎዳና ላይ ብወጣ እንደኔ ያሉ መሰል ወጣቶች የቁስሌ ተካፋይ ሊሆኑ ይችላሉ” የሚል እሳቤ በውስጧ አደረ፡፡ ከሁለት ዓመታት በላይም በዚህ የሕይወት መንገድ አለፈች፡፡ ይህም ከፆታዊ ጥቃት እስከ ሱስ ተጋላጭነት ለደረሰ ዘርፈ ብዙ ጉዳት እንድትዳረግ እንደዳረጋት በልብ መሰበር ውስጥ ሆና ታስታውሳለች፡፡ 

“ተስፋ ማጣት የሰውን ልጅ ስለነገ ህይወቱ እንዳያስብ ያደርገዋል” የምትለው ወጣት ቤተልሄም፤ “ህይወት ሲከፋብኝ፣ የቅርብ አይዞሽ ባይ ቤተሰብ ከጎኔ አለመኖራቸው ትዝ ሲለኝ፣ በበዛ ትካዜ ውስጥ እዋጣለሁ፡፡ ለምንድ ነው አሁን እየኖርኩ ያለሁት? በቃ አብቅቶልኛል፡፡ የእድሜዬን ወሳኝ ጊዜ በአዲስ አበባ ጎዳና ላይ ነው ያሳለፍኩት በማለት እሰበራለሁ። ከዚህ በኋላ የትኛው የሕይወት መስመር ወደ ቀናው መንገድ ይወስደኝ ይሆን? የሚል ጥያቄ በውስጤ ይመላለሳል፡፡ ብዙ ጊዜ በእንደዚህ አይነት የተደበላለቀ ሃሳብ ውስጥ እራሴን አገኘዋለሁ፡፡ ለጥያቄዎቹ እርግጠኛ የሆነ መልስ የመመለስ አቅም አልነበረኝም፡፡” በማለት ከባዱን የሕይወቷን እውነት ታስረዳለች፡፡ 

ትምህርቷን ከ10ኛ ክፍል ላቋረጠችው፣ መማሪያ ደብተሮች በመያዝ ፈንታ የስጋት ሕይወትን አንድ ሁለት ብላ መለማመድ የግድ ላላት ለዚህች ወጣት፤ ከእለታት በአንዱ ቀን የወጣላት ብርሃን ዳግም ሕይወቷ እንዳይጨልም አድርጎታል። ተስፋ በማይሰጠው፣ ብርድ፣ ጸሐይ  እና ዝናብ በሚፈራረቅበት የጎዳና ሕይወት ብትቆይም የመከራዋ ማብቂያ ቀን ላይ ጸሐይ ወጥቶላታል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን በማብቃት፤ በከተማዋ እያንዳንዱ እንቅስቃሴና ልማት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ በማድረግ ረገድ ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሁነኛ ተጠቃሽ ነው፡፡

“ወደ ማዕከሉ ከመግባታችን በፊት የጤና ምርመራ በማድረግ አንድ ብለን የጀመርነው የተቃናው መስመር ጉዞ ፍፃሜውም የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ፤ ለዘመናት ደርቆ የነበረውን የሰዎች ጉስቁልናና ጉዳት ዳግም እንዲያንሰራራ የሚያደርግ የምንጭ ውሃ ነው የሆነልን” የምትለው ቤተልሄም፣ “ወደ ማዕከሉ ከገባን ጀምሮ የራሳችን የሆነ አልጋ፣ ቢጃማ እንዲሁም ሴት ልጅ ያስፈልጋታል ተብሎ የሚታሰቡ ነገሮች ጭምር ተሟልቶልን ቆይታ አድርገናል። ተስፋ ሰጪ እና ሕይወታችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ሊያሸጋግሩ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን መውሰድ ችለናል” በማለት ሃሳቧን አክላለች፡፡ 

ወጣት ቤተልሄም በማብራሪያዋ፤ “የህይወት ክህሎት፣ የስነ ልቦና እንዲሁም የሙያ ስልጠና ለስድስት ወራት ያክል ወስጃለሁ፡፡ ማዕከሉ በተለያዩ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ ወጣት ሴቶች ያደረገው ድጋፍ እንደ ግለሰብ ብቻ የሚታይ ተግባር ሳይሆን ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የሴቷ ሚና ሲታከልበት እጅግ የላቀ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ እኔም የወሰድኳቸው ስልጠናዎች ካሉብኝ ማኅበራዊ ብሎም ኢኮኖሚያዊ ችግሮቼ እንድወጣ አግዞኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ሴቶች አይደፍሩትም በሚባለው የሳኒተሪ (የቧንቧ ጥገና ዘርፍ) የመጀመሪያ ዙር ሰልጣኝ በመሆን ወስጃለሁ፡፡ አሁን ላይ በማዕከሉ ውስጥ በቧንቧ ጥገና ዘርፍ የስራ እድል ተፈጥሮልኝ እየሰራሁ እገኛለሁም ብላለች፡፡

በተለይ እንደነዚህ ያሉ የሙያ መስኮች ላይ ለመሰልጠን ሴቶች እምብዛም አይደፍሩትም፡፡ የሙያ ስልጠናውን እንድትወስድ ያደረጋት ሴት ልጅ ከልቧ ከቆረጠችና ካሰበች ትችላለች የሚለውን የህይወት ክህሎት ስልጠና ካገኘች በኋላ እንደነበር ተናግራለች፡፡ የሲኦሲ (COC) ፈተናዋን በብቃት በመወጣትም ግንባር ቀደም ሰልጣኝ ለመሆን ችላለች። የተሻለ ሕይወትን ለመምራት ከዚህ የበለጠ እድል እንደማይመጣ በመረዳቷ የተሰጣትን እድል አላባከነችም፡፡ በማዕከሉ የተመቻቸላትን እድል ወደ ውጤት ከመነዘሩት አንዷ የሆነችው ይህችው ወጣት በሰለጠነችው ሙያ መስራት ከጀመረች አንድ ዓመት ከሁለት ወር ገደማ ሆኗታል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ለዓመታት ስትናፍቃትና በጉጉት ስትጠባበቃት የነበረችውን እናቷን ማዕከሉ አፈላልጎ አግኝቶላታል፡፡ “እናቴ ማነች?” የሚል የዓመታት ጥያቄዋ ተመልሷል፡፡ አሁን ላይ ቤት ተከራይታ እየኖረች፣ የወር ገቢ የምታገኝበትን ሥራም እየሰራች ትገኛለች።

ወጣት ቤተልሄም ከ10ኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርቷን ለመቀጠል ትልቅ ራዕይ ሰንቃለች፡፡ በቁጭት መንፈስ ትምህርቷን ከዳር በማድረስ እንደ እርሷ ጎዳና ላይ የወጡ እህቶቿን ሕይወት የማስተካከል እቅድ አላት፡፡ በተለይም የጎዳናን አስከፊነትን በማስረዳት የትኛዋም ሴት የሕይወት አማራጯ እንዳታደርገው ተሞክሮዋን በማስረዳት ጭምር በርካቶችን የመታደግ ዓላማ አንግባለች፡፡

በመዲናችን አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ለነገዋ የሴቶች የተሀድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት መመረቁ የሚታወስ ነው፡፡

ማዕከሉ በተመረቀበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት ላይ፣  ፕሮጀክቱ እንደ ሀገር ያሉብንን ስብራቶች ለመጠገን እድል ይሰጣል፡፡ ልጆች ወልደን፣ ተንከባክበን አስተምረን ለወግ ማዕረግ ማብቃት ሲገባን፤ ባሉብን ዘርፈ ብዙ ድካሞች አማካኝነት  ለጎዳና እና ላልተገባ የሕይወት ዘይቤ ሲዳረጉ እነርሱን መልሶ የሕይወት መስመራቸውን ማቅናት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም  በድህነት ምክንያት አውራ ጎዳና ላይ ወጥተው ባልተገባ መንገድ ሕይወታቸውን የሚመሩ ሴቶችን ከዚህ መንገድ መመለስ የእነሱን ሕይወት ብቻ መመለስ አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ያለብንን አርቆ የማሰብን ስብራት ለመጠገን ማዕከሉ በእጅጉ እንደሚያግዝ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ከሰሞኑ በአራተኛው ዙር የማዕከሉ ተመራቂዎች መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ “በሰው ሕይወት ላይ ለውጥ የማያመጣ ልማት የተሟላ ሊሆን አይችልም። አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነባት እንዲሁም ለዘመናት የከረሙ ስብራቶቿ የሚጠገኑባት የማድረግ ተግባራችን ጣፋጭ ፍሬ እያፈራ ነው። ለዚህም አንዱ ይኸው ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ወደ አገልግሎት ከገባበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት ውስጥ ሆነው ተስፋ ለቆረጡ ሴቶች አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ከፋች ሆኗል። ትላንት በጎዳና፣ በችግር እና በተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶች ዛሬ ራሳቸውን ችለው ለተሻለ ሕይወት እንዲበቁ እያስቻለ ያለ ማዕከል ነው።

ተመራቂ ሴቶችንም፣ “አስከፊው ትላንታችሁ አልፏል፤ በማዕከሉ በነበራችሁ ቆይታ በቀሰማችሁት ክህሎት እና ባገኛችሁት የተሀድሶ ስልጠና ዛሬን ማሸነፍ ችላችኋል፤ ነገም በስራው ዓለም ለሚገጥማችሁ ማንኛውም ፈተና እጅ ሳትሰጡ ህይወታችሁን ይበልጥ ብሩህ እንደምታደርጉ አምናለሁ።” ሲሉ አክለዋል፡፡

“ሴቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች ንቁ ተሳታፊ ማድረግ ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና ትልቅ አስተዋፅኦ አለው” ያሉት ደግሞ የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ዳይሬክተር  ሂርጳሳ ጫላ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ማዕከሉ በከንቲባ አዳነች አቤቤ ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረ ሰው ተኮር ፕሮጀክት ነው፡፡ ዋናው ዓላማው በብዙ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን በመለየት የተሃድሶ ስልጠና ይሰጣል። ከዚያም የሙያ ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ አድርጎ ወደ ስራ በማሰማራት እራሳቸውን በኢኮኖሚ ማስቻልን ታሳቢ አድርጎ የተቋቋመ ማዕከል ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

ሂርጳሳ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው፤ በአንድ ዓመት ከ9 ወር ቆይታ ውስጥ ማዕከሉ በአራት ዙር 2 ሺህ 401 ሴቶችን አስመርቋል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም የ5ኛ ዙር ሰልጣኞችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም፤ ጤናማ፣ ምርታማና የተረጋጋ ከተማን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ሴቷ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች፡፡ ማዕከሉም በተለይም በጎዳና ሕይወት፣ በንግድ ወሲብ ሥራ እና በሌሎች ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ የነበሩ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ሰልጣኞች በቅድሚያ የጤና ምርመራ እንዲያከናውኑ የሚደረግ ሲሆን የህይወት ክህሎት፣ የስነ ልቦና እና የሙያ ስልጠናዎችን ያገኛሉ። መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ከሟሟላት አንፃርም የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመቆያ ክፍሎች፣ የጤና እንክብካቤ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የሥልጠና ወጪያቸው እንዲሁ ይሸፈንላቸዋል። ስልጠናቸውን ጨርሰው ከማዕከሉ በሚወጡበትም ጊዜ አነስተኛ የማቋቋሚያ፣ ወደ ስራ ከተሰማሩ በኋላ የሙያ እንዲሁም የአስተዳደራዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ ዋናው ዓላማ ሴቷ ከነበረባት ችግር ተላቅቃ እራሷን እንድትችልና በሁለት እግሮቿ እንድትቆም ለማድረግ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እስካሁን በተሰሩ ሥራዎች የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ሂርጳሳ (ዶ/ር) ሲያስረዱ፣ “በዋናነት በብዙ ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ የነበሩ ሴቶች ከኢትዮጵያዊ ስርዓትና እሴት ውጪ ሆነው ይሰሩት ከነበረው ስራ ተላቅቀውና ጤናማ በሆነ ስራ ላይ ተሰማርተው እንዲሰሩ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በላባቸው እና በድካማቸው ሰርተው መተዳደር እንደሚችሉ ግንዛቤያቸው አድጓል፡፡ በጥቅሉ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ልህቀት ማበልጸጊያ ማዕከል ጤናማ እና ምርታማ ከተማ ለመገንባት በሚደረገውን ጥረት ትላልቅ ተሰፋ ሰጪ ሥራዎችን እየከወነ ይገኛል” ብለዋል፡፡

ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ነው፡፡ በዓሉ “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነት እና ለበለጸገች ኢትዮጵያ!” በሚል መሪ ሀሳብ በሀገራችን ለ50ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል፡፡ ቀኑን ከማክበር ባለፈ የሴቶችን ተጠቃሚነት እና በከተማ ብሎም በሀገር ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በተግባር በማረጋገጥ ረገድ የተጀመሩትን ሥራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል እንላለን፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review