በውቧ አዲስ አበባ የ5 ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ በድምቀት ተካሂዷል

You are currently viewing በውቧ አዲስ አበባ የ5 ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ በድምቀት ተካሂዷል

AMN – የካቲት 29/2018 ዓ.ም

50ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በአዲስ አበባ በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በድምቀት ተካሒዷል፡፡

ፕሮግራሙን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ከሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።

ሩጫው ከውድድርነት ባለፈ ሴቶች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ያላቸውን የእኩልነት ጥያቄ ለማንጸባረቅ ያለመ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኝው የዘንድሮው የሴቶች ቀን “የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከበረ ይገኛል።

መርሐ ግብሩን በይፋ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ቡዜና አልከድር እና የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።

ጀግኖቹ አትሌቶች መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባና እጅጋየሁ ዲባባ እንዲሁም በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሴቶችና አካል ጉዳተኛ ሴቶችን ጨምሮ ከ100 ሺህ በላይ ሴቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

መነሻውን ከአትላስ አካባቢ ያደረገው የ5ኪ.ሜ ሩጫ ውድድር ፍጻሜውን የሴቶች አደባባይ ያደረገ ሲሆን፣ አካል ጉዳተኛ ሴቶችም የ2 ኪሎ ሜትር ውድድር አካሒደዋል፡፡

በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ድረስ ለወጡ አትሌቶችም የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review