AMN መጋቢት 3/2018
የአፍሪካ የሚዲያ ባለሙያዎች የአህጉሪቷን ትርክት የመቅረጽ ሚናቸውን በተጠናከረ መልኩ ሊወጡ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አሳሰቡ።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በህብረቱ የመገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ድጋፍ ፕሮግራም (AU Media Fellowship) ከታቀፉ የሚዲያ ባለሙያዎች ጋር በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል።
ከ18 የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡት 22 ባለሙያዎች በፕሮግራሙ አማካኝነት ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት እና ቁልፍ አጋሮች ጋር ያላቸውን የጥናት ጉዞ እና ቆይታዎች ጀምረዋል።
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር የአፍሪካ ጋዜጠኞች የአህጉሪቷን ትርክት ከመቅረጽ አንጻር ያላቸውን ቁልፍ እና ጠንካራ ሚና አንስተዋል።
የአፍሪካ መጻኢ ጊዜ ተረክ ሊጻፍ የሚገባው በአፍሪካውያን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዩሱፍ የሚዲያ ባለሙያዎቹን ስብስብ በፕሮግራሙ በመካተታቸው እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ባለሙያዎቹ አፍሪካ በአጀንዳ 2063 ስር ያላትን ትልሞች የሚያንጻባርቁ ጠንካራ እና መፍትሄ ተኮር የይዘት ስራዎችን ለማከናወን ያላቸውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
በአፍሪካ ህብረት የመገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ድጋፍ ፕሮግራም የታቀፉ የሚዲያ ባለሙያዎች የአፍሪካን ድምጽ በማጉላት እና ህብረቱ ከዜጎች ጋር በማስተሳሰር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ኤኤምኤን ከህብረቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የሙያዊ ድጋፍ ፕሮግራም የአፍሪካ ሚዲያ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች እና ይዘት ፈጣሪዎች አቅም በመገንባት ዘመኑ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመው አህጉራዊ ልማት ተኮር ዘገባዎችን እንዲሰሩ የማድረግ አላማ ያለው ነው።
እ.አ.አ በ2022 የተጀመረው ፕሮግራም ሙያዊ ክህሎትን ማሻሻል፣ ትስስር እና ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም የሚዲያ ቴክኖሎጂ ተደራሽነታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ የፕሮግራሙ አበይት ትኩረቶች ናቸው።
ለአንድ ዓመት የሚቆየው ፕሮግራም ስልጠናዎች፣ የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት፣ ሙያዊ ጉብኝቶች፣ በትላልቅ ሁነቶች ላይ መሳተፍ፣ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይቶችን የማድረግ እድል ማግኘት እና ባለሙያዎቹ ለሚሰሯቸው ዘገባዎች የሚያስፈልጓችውን ግብአቶችን ማሟላት ጨምሮ ተጓዳኝ ጉዳዮችን ያካተተ ነው።