AMN- መጋቢት 4/2018 ዓ.ም
በዓለማችን የቴክኖሎጂ እድገት የመንግስትን አሰራር ግልጽና ቀልጣፋ ከማድረግ ባለፈ፣ ለዘመናት ስር የሰደደውን ሌብነትና ሙስና ለመዋጋት ዋነኛ መሳርያ እየሆነ መጥቷል።
በተለይም የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን ተግባራዊ ያደረጉ ሀገራት፣ በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ሀብትን ከምዝበራ ማዳን መቻላቸውን ተሞክሮዎች ያሳያሉ።
በዚህ ረገድ ቀዳሚ የምትባለው ኢስቶኒያ፣ 99 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿን በዲጂታል መታወቂያ በማስተሳሰር ድንቅ ስኬት አስመዝግባለች።
ሀገሪቱ በየዓመቱ ከአጠቃላይ ምርቷ (GDP) 2 በመቶ የሚሆነውን ወጪ ማዳን የቻለች ሲሆን፣ ይህም በወረቀትና በሰው ኃይል ይባክን የነበረውን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠቧ የመጣ ነው።

ኢስቶኒያ አሁን ላይ “Bürokratt” የተባለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ረዳትን በመጠቀም ዜጎች በአካል ሳይገኙ አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገች ትገኛለች።
በሌላ በኩል፣ ህንድ “አዳር” (Aadhaar) የተባለውን የዓለማችን ግዙፍ የባዮሜትሪክ ስርዓት በመዘርጋት ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትርፍ አግኝታለች። ቀደም ሲል በሌሉ ወይም በሞቱ ሰዎች ስም ይባክን የነበረውን የቢሊዮን ዶላር የመንግስት ድጎማ ማስቀረት ችላለች። ይህም 5 መቶ ሚሊዮን አዳዲስ የባንክ አካውንቶች እንዲከፈቱና ድሆች የፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል።

ሲንጋፖር በበኩሏ “ሲንግፓስ” (Singpass) በተባለ ዲጂታል ቁልፍ አማካኝነት ከ2ሺ 700 በላይ አገልግሎቶችን በማቀላጠፍና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር ረገድ በዓለም የሳይበር ደህንነት ቀዳሚ ሆናለች። ዩክሬንም “Diia” በተባለ መተግበሪያ የግንባታ ፈቃድና የንግድ ስራ ቢሮክራሲን በማቃለል ሙስናን መቀነስ ችላለች፡፡

ኢትዮጵያም ይህንን የዓለም ተሞክሮ መሰረት በማድረግ “ፋይዳ” (Fayda) የተባለውን ብሄራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት እንደ ዋና የዲጂታል ኢኮኖሚ ምሰሶ እየተገበረች ትገኛለች።
ስርዓቱ በተለይ በባንክ ዘርፍ የሚፈጸሙ የማንነት ማጭበርበሮችን ለማስቀረትና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር ትልቅ ተስፋ ጥሎበታል።
ከዚህ በተጨማሪም እንደ “ሴፍቲኔት” ያሉ ማህበራዊ ድጋፎች በመካከለኛ አካላት ሳይመነተፉ በትክክል ለሚገባቸው ዜጎች እንዲደርሱ ለማድረግ ፋይዳ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው።
መንግስት የዲጂታል መታወቂያ አዋጅን በማጽደቅ፣ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም ዜጎች የዚህ ስርዓት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
በአጠቃላይ ዲጂታል መታወቂያ የቴክኖሎጂ ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ የመንግስትን አሰራር ግልጽና ተጠያቂ በማድረግ የሀገርን ሀብት ለመጠበቅ የሚያገለግል ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ነው።
በቶለሳ መብራቴ