የፊንጥጣ ኪንታሮት እንዴት ይከሰታል? የሕመሙ ምልክት እና ሕክምናውስ?

You are currently viewing የፊንጥጣ ኪንታሮት እንዴት ይከሰታል? የሕመሙ ምልክት እና ሕክምናውስ?
  • Post category:ጤና

AMN – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም

በፊንጢጣ አካባቢ የሚወጡ ኪንታሮቶች ወይም በሕክምናው መጠሪያ “ኮንዲሎማ አኩሚናታ” በመባል የሚታወቁት የጤና እክሎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ።

የፌንጥጣ ኪንታሮት በአብዛኛው የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ (HPV) ተብሎ በሚጠራው ተላላፊ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን፣ በሽታው ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈውም በዋነኝነት በግብረ-ሥጋ ግንኙነትና በቀጥታ በሚደረግ የቆዳ ንክኪ መሆኑን በየካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ የቀዶ ህክምና ሀኪም ዶ/ር ወንድወሰን አምታታው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

እንደ ዶ/ር ወንድወሰን ገለጻ፣ የፌንጥጣ ኪንታሮት ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ከገባ በኋላ ወዲያውኑ ምልክት ላያሳይ ይችላል።

ሆኖም ግን ከሳምንታት ወይም ከወራት በኋላ በፊንጢጣ ዙሪያና በውስጠኛው ክፍል ላይ የተሰባሰቡ ወይም የተበተኑ ትናንሽ እብጠቶች መታየት ይጀምራሉ ብለዋል።

እነዚህ እብጠቶች አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ የማሳከክ ስሜት፣ ምቾት ማጣት እና አልፎ አልፎም ደም የመፍሰስ ሁኔታ ሊታይባቸው እንደሚችል ዶ/ር ወንድወሰን አብራርተዋል።

ይህ የጤና እክል በራሱ ጊዜ የመጥፋት እድሉ አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ዶ/ሩ፣ ምልክቱ የታየባቸው ግለሰቦች ሳይዘገዩ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በአሁኑ ወቅት የፌንጥጣ ኪንታሮትን ለማከም የተለያዩ የሕክምና አማራጮች ያሉ ሲሆን፤ በሐኪም ትዕዛዝ መድኃኒት በመቀባት፣ ኪንታሮቱን በፈሳሽ ናይትሮጅን በማቀዝቀዝ ማርገፍ፣ በኤሌክትሪክ ሙቀት ማቃጠል ወይም ሁኔታው የከፋ ከሆነ በቀዶ ጥገና ማስወገድ ህክምናዎች እንደሚሰጡ ዶ/ር የወንድወሰን አስገንዝበዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ ተደብቆ የመቆየት ባህሪ ስላለው፣ ኪንታሮቱ ቢወገድም እንኳ ተመልሶ የመውጣት እድል ስላለው ተከታታይ የሕክምና ክትትል ማድረግ አስፈላጊ ነው።

በሽታውን ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ስርጭቱን ለመቀነስ ዋነኛው መከላከያ መንገድ የኤች.ፒ.ቪ ክትባትን መውሰድ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ማድረግ እና የግል ንፅህናን መጠበቅ ወሳኝ ናቸው።

የፌንጥጣ ኪንታሮት በወቅቱ ካልታከመ ከከፋ የጤና ችግር አልፎ ለፊንጢጣ ካንሰር ሊያጋልጥ ስለሚችል፣ ኅብረተሰቡ ስለ በሽታው ያለውን ግንዛቤ በማሳደግና ምልክቶች ሲታዩ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ ራሱን ከከፋ አደጋ ሊከላከል እንደሚገባ ዶ/ር ወንደወሰን አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review