“መራጩ ምርጫ ባህል መሆን እንዳለበት በማመን መሳተፍ ይኖርበታል”
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ደያሞ ዳሌ
በየቀኑ ምን መስራት፣ ምን መልበስ፣ ምን መመገብ፣ የት መሄድ… እንዳለባችሁ ሌላ ሰው የሚወስንላችሁ ቢሆን ምን ይሰማችኋል? ደስተኛ ትሆናላችሁ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በተመሳሳይ ነጋችሁንም ራሳችሁ ነው መወሰን ያለባችሁ። ነጋችሁ ምን መምሰል እንዳለበት፣ ምን እድል እንዳላችሁ፣ ምን ዓይነት የጤና እና የትምህርት ሥርዓት ማየት፣ በምን ዓይነት ሥርዓት ውስጥ መኖር እንደምትፈልጉም በራሳችሁ መወሰን ትፈልጋላችሁ። በምርጫ መሳተፍን አስፈላጊ የሚያደርገው ይህ ምክንያት እንደሆነ “የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለፍትሐዊ ምርጫና ዴሞክራሲ” የተሰኘውን ተቋም በሥራ አስፈጻሚነት የመሩት እና የምርጫ ጉዳይ ባለሙያዋ ኑኖ ዶልዲዝ ይናገራሉ፡፡
“Your vote, your voice: why every vote matters” በሚል ርዕስ “UN Today” በተሰኘው የገፀ ድር ጋዜጣ ላይ ዶልዲዝ በሰጡት ማብራሪያ፣ “ምርጫ መኖር የምንፈልግባትን ዓለም በመወሰን ወይም ተፅዕኖ በማሳረፍ ጉልህ ፋይዳ አለው። አንዳንዶች የአንድ ሰው ድምፅ ምንም ለውጥ አያመጣም ይላሉ። ነገር ግን አስር ሰዎች ወይም መቶ ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ቢያስቡስ? ይህ ማለት አስር ድምፅ ወይም መቶ ድምፅ ባከነ ማለት ነው። በታሪክ ውስጥ የአንድ ሰው ድምፅ የውሳኔውን ውጤት የለየባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ስለዚህ ያቺ ወሳኝ ድምፅ ያንተ/ያንቺ ልትሆን ትችል ነበር” ይላሉ፡፡
በኢትዮጵያም 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ለዚህም በምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመወዳደሪያ ምልክትና ማንፌስቷቸውን እያስተዋወቁ ነው። በተለያዩ ጉዳዮች ላይም በመገናኛ ብዙኃን ክርክሮችን እያካሄዱ ይገኛል። ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የመራጮች ምዝገባ ጀምሯል፡፡ ከዚህ አኳያ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊ፣ ነጻና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ከሕዝብ ምን ይጠበቃል? ስንል የከተማዋን ነዋሪዎች፣ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና መረጃዎችን በማካተት ለመዳሰስ ሞክረናል፡፡
“ምርጫ የሕዝብን ጥያቄዎች የሚመልስና ሀገርን በቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራ አካልን የምንወስንበት ጉዳይ በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ አዳዲስ ሐሳብና አጀንዳ በመያዝ የሚቀርቡበትና ከዚህ ውስጥ የተሻለ ሀገርን የሚያራምድ ሐሳብ ያለውን የምንመርጥበት ነው” ይላሉ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ የሆኑት አቶ ጉዲና አበሽሎ፡፡

ከዚህ ቀደም በተካሄዱ ምርጫዎች በመራጭነት ለአራት ጊዜ ያህል መሳተፋቸውን የነገሩን አቶ ጉዲና፣ በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚዲያ እያካሄዱት ያለውን የምርጫ ክርክር እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሌላኛው አስተያየቱን ያጋራን ወጣት በረከት አበራ ይባላል፡፡ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ነዋሪ ነው፡፡ ወጣቱ እንደሚናገረው፣ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ አሸናፊ ሆኖ ሀገርን የሚያስተዳድር አካል የሚመረጥበት ወሳኝ ሂደት በመሆኑ ካርድ በማውጣት ድምፅ መስጠት እንደ ዜጋ ኃላፊነትን መወጣት ነው፡፡ የአንድ ሰውም ድምፅ በምርጫ ዋጋ አለው፡፡
በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ መሳተፉን የሚናገረው ወጣት በረከት፣ “በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ‘ይጠቅመኛል፤ ለሀገርና ሕዝብ ይበጃል፤ ሀገርን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ይሠራል’ የምለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ። ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ፖሊሲና ፕሮግራም ይዘው እንደቀረቡ በቴሌቪዥን መስኮትና በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የፓርቲዎች የክርክር መድረኮችን እየተከታተልኩ ነው፡፡ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም ከገዥው ፓርቲ ባለፈ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ሕዝቡ ከሁሉም በላይ ሰላምን በማስቀደም መንቀሳቀስ ይገባቸዋል” ሲል ሐሳቡን አጋርቷል፡፡
ሌላው የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ረሻድ አብደላህ እንዲሁ ምርጫው “በሕይወታችን የተሻለ ለውጥ ያመጣልናል” ብለን የምናስበውን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ኃላፊነት የምንሰጥበት ነው፡፡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ ለመስጠትም ከወዲሁ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የምርጫ ፉክክሮችን እየተከታተሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ደያሞ ዳሌ ግሎባል ፒስ ባንክ በተሰኘ በሰላም ግንባታ ዙሪያ በሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም የሰላም ግንባታና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር እና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚናገሩት፣ ምርጫ የአንድ ሀገር ዜጎች የሚያስተዳድራቸውን፣ ሕግ የሚያወጣላቸውን፣ የሚወስንላቸውን ሰዎች የሚመርጡበትና የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን የሚያሳዩበት ሂደት ነው፡፡ ምርጫ የሚካሄደው ሰላማዊና ተአማኒነት ያለው የፖለቲካ ሽግግር ሂደት እንዲኖር ነው፡፡ ምርጫ ለማካሄድ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ በምርጫው የሚሳተፉ ተዋናዮች ምርጫን በተመለከቱም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች መሠረት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

አቶ ደያሞ እንደሚሉት፣ በምርጫ ድምፅን መስጠት የዜግነት ግዴታ ሆኖ መታየት አለበት፡፡ ለዚህም ሕዝቡ የምርጫ ካርዱን መውሰድና ድምፁን ለመስጠት ዝግጁ መሆን ይኖርበታል፡፡ የምንተቸውን፣ የምንወቅሰውን ለመቀየር ወይም ጥሩ ሠርቷል ወይም የተሻለ ሐሳብ አለው ብለን የምናምንበትን ለመደገፍ ምርጫ ወሳኝ ነው፡፡ ምርጫ ተጠያቂነትን ለማምጣት ያስችላል፡፡ ለዚህም ሁሉም ዜጋ በነቂስ በመውጣት የዜግነት ጉዳይ አድርጎ የምርጫ ካርድ መውሰድ አለበት።
ሌላው ከሕዝብ የሚጠበቀው በምርጫው የሚወስነው ውሳኔ በእውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን የፓርቲዎችን አቋም ማወቅ ነው፡፡ ለዚህም የምርጫ የክርክር መድረኮችን መከታተል ይጠበቅበታል፡፡ እንዲሁ በደፈናው ድምፅ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመረዳት የተሻለ የሚለውን በማነጻጸር መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ ‘ይህን ፓርቲ የምመርጠው በዚህ ምክንያት ነው፤ አቋሙ ይኼ ነው’ ለማለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምሳሌ በትምህርት፣ በውጭ ጉዳይ፣ በጤና እና በተለያዩ ጉዳዮች ያላቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ የምርጫ ማኒፌስቷቸውን፣ እርስ በርስ የሚያደርጉትን ክርክርና ፉክክር መከታተል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመገናኛ ብዙኃን ባሻገር በቀጣይ በየቦታው በመንቀሳቀስ የሚያደርጉትን የምርጫ ቅስቀሳ መከታተልም ከሕዝብ ይጠበቃል። መራጩ ምርጫ የሰላም መሠረት መሆኑን፣ ሰላማዊ ፖለቲካ እንዲፈጠር ምርጫ ባህል መሆን አለበት የሚለውን በማመን መሳተፍ እንዳለበት አቶ ደያሞ ያነሳሉ፡፡
“በምርጫው ላይ በማህበራዊ ሚዲያ የተለያዩ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ አስተያየቶች ሊሰነዘሩ፤ ብዙ ግርግሮችም ሊታዩ ይችላሉ፡፡ ዋናውና ወሳኙ መሬት ላይ የሚሠራው ነው። ከዚህ አኳያ ሕዝቡ ከአሉባልታዎች ራሱን በመጠበቅ ምርጫው ሰላማዊ፣ ነጻ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ መወጣት ይኖርበታል፡፡ ሀገር ሰላም የምትሆነው፤ ብዙ ነገር የምናስተካክለው የምርጫ ሥርዓቱን ስንቀበል ነው፡፡ የሚጎድለንን ነገር እያሟላን እንሄዳለን፡፡ በምርጫ ካልተሳተፍን የምናመጣው ለውጥ የለም። ምርጫ የሰላም መሠረት ነው፡፡” ሲሉ ምሁሩ አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ምርጫ የሚካሄደው በእያንዳንዱ የምርጫ ክልል ለምሳሌ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሆነ በ100 ሺህ ሕዝብ አንድ የሚወክል ሰው ለመምረጥ ነው፡፡ “የእኔ ድምፅ አንድ ቦታ ብቻ ነው ዋጋ የሚኖረው፤ ሌላ ቦታ የሚያሸንፈውን የሚወስነው ሌላው መራጭ ነው” በማለት ከምርጫ ራስን ማግለል አይገባም፡፡ እያንዳንዷ ድምፅ ዋጋ አላት፡፡ የምንፈልገው እንደሚያሸንፍ አምነን ብቻም ሳይሆን ‘ድምፄ ዋጋ አለው፤ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ’ በሚል ተረድተን ድምፅ መስጠት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡
በስንታየሁ ምትኩ