የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት የቀረበ የሀገራዊ ምክክር ጥሪ አቅርቧል።

You are currently viewing የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት የቀረበ የሀገራዊ ምክክር ጥሪ አቅርቧል።

የጥሪውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል!

~~~~~||~~~~

ለትግራይ ክልል ባለድርሻ አካላት የቀረበ የሀገራዊ ምክክር ጥሪ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገራችን እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለሚታዩ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መንስኤዎችን በመለየት፤ በምክክር መግባባት ላይ እንዲደረስባቸውና ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተቋቋመ ኮሚሽን ነው። ኮሚሽኑ በሂደት ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክር አሳታፊና አካታች እንዲሆን ለማድረግ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል። በዚህም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከወረዳ ጀምሮ እንዲካተቱ ለማድረግ ሰፊ ጥረት አድርጓል።

በሂደቱ ለመሳተፍ ፍቃደኛ የሆኑ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቋማትና ማህበራት፣ ምሁራን፣ እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት እንዲካተቱና ትርጉም ያለው ተሳተፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ያስቻሉ በርካታ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቷል። ነጻና ገለልተኛ ሆኖ በተቋቋመበት አዋጅ መሠረት ሥራዎቹን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የትግራይ ክልልንም እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ክልሎች ሁሉ ለማካተትና ለማሳተፍ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።

በሰሜኑ የሀገራችን አከባቢ ተከስቶ የነበረው ጦርነት ኢትዮጵያን ለጉዳት የዳረገ መሆኑ ይታወቃል። ጦርነቱ በተደረሰው ስምምነት መሠረት መቋጫ ካገኘ በኋላም የድህረ ጦርነት ሁኔታዎች በተለያየ መልኩ ሊገለጹ የሚችሉ ማህበራዊ እና ሌሎች ችግሮች እንደፈጠሩ ኮሚሽኑ ይረዳል።

በሌላ በኩል በሂደት ላይ ያለው ሀገራዊ ምክክር በሀገራችን ኢትዮጵያ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ብቸኛ አማራጭ ሆኖ የቀረበበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። በትግራይ ክልል የሚገኙ ኢትዮጵያውን ዜጎቻችን በዚህ ታላቅ ሂደት የመካተትና የመሳተፍ ሙሉ መብትና ኃላፊነትም ያለባቸው ከመሆኑም ባሻገር ለውጤታማነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ኮሚሽኑ ይገነዘባል።

ከዚህም በመነሳት ኮሚሽኑ የትግራይ ክልል በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፍ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር፣ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የተለያዩ ተቋማትና ማህበራት፣ ከምሁራንና ታዋቂ ሰዎች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይነት ያላቸው ከ22 በላይ ውይይቶችን በመቐለ እና አዲስ አበባ አካሂዷል። በእነዚህ ውይይቶች ምክክሩ የክልሉንም ሆነ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችል መግባባት ላይ የተደረሰ ቢሆንም፤ ኮሚሽኑ ባለው የአሰራር ሥርዓት መሠረት በክልሉ ተሳታፊዎችን የመለየትና አጀንዳ የማሰባሰብ ተግባር ለማከናወን የሚረዳ አስቻይ ሁኔታ ባለመፈጠሩ፤ የትግራይ ክልል ሕዝብና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተወካዮቻቸው አማካኝነት የሚሳተፉበት የአጀንዳ ማሰባሰብና የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተሳታፊዎች ልየታ መድረክ ከመጋቢት 23 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ እንዲካሄድ የኮሚሽኑ ምክር ቤት ወስኗል።

በመሆኑም የትግራይ ክልል ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቋማትና ማህበራት፣ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች፣ እንዲሁም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርና በየደረጃው የምትገኙ የክልሉ የመንግሥት አካላት ኮሚሽኑ እያቀረበ ባለው ጥሪ መሠረት በመድረኩ በመሳተፍ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትውጡ ኮሚሽኑ የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።

በዚሁ አጋጣሚ በመላው ሀገራችን የምትገኙና በተለያዩ ምክንያቶች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ሳትሳተፉ የቆያችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታጣቂ ኃይሎች እና ሌሎችም ወገኖቻችን በዚህ ታሪካዊ ሂደት ለመሳተፍና የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍቃደኛ በሆናችሁበት እና አስቻይ ሁኔታዎች በተፈጠሩበት ጊዜ ሁሉ ለሚኖራችሁ ተሳትፎ የኮሚሽኑ ምክር ቤት በር ሁልጊዜም ክፍት መሆኑን እየገለጸ ለዚህም እውን መሆን እስከአሁን ኮሚሽኑ ያደረጋቸውን ጥረቶች ይበልጥ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም በድጋሚ ያረጋግጣል።

በመጨረሻም በሀገራችን የሚታዩ እጅግ መሠረታዊና ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ላይ በመካከርና መግባባት ላይ በመድረስ ሁላችንም በጋራ የምንኖርባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የትግራይ ሕዝብ ተሳትፎም አስፈላጊ በመሆኑ ኮሚሽኑ የተከበረው የትግራይ ሕዝብና ባለድርሻ አካላት በመድረኩ እንዲሳተፉ ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review