ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየተጋች ነው

You are currently viewing ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየተጋች ነው

AMN — መጋቢት 20/2018 ዓ.ም

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር ከአፍሪካ ቀዳሚ ለመሆን እየተጋች እንደምትገኝ አስታወቀ፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በርኦ ሀሰን እንደገለጹት፤ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ወደ 140 ሺህ የሚጠጉ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

ይህን ተከትሎም በአገር ውስጥ ተሽከርካሪዎችን የሚገጣጠሙ 17 ያህል ተቋማት እንዲፈጠሩ ማስቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመሠረተ ልማት ዝርጋታውን ለማሳለጥ መንግሥት በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ 2,300 ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ማቀዱን አቶ በርኦ ጠቁመዋል።

ይህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግር በከተሞች የሕዝብ ትራንስፖርት ላይም ትልቅ ለውጥ እያመጣ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ከተሞች የኤሌክትሪክ አውቶብሶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

በአዲስ አበባ ብቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግሥትና በግል አጋርነት ከመቶ በላይ የኤሌክትሪክ አውቶብሶች ወደ ሥራ መግባታቸውም ተመላክቷል።

ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ የራሷን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ብራንድ ለዓለም ለማስተዋወቅ ለያዘችው ትልቅ ራዕይ እንደ መጀመሪያ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ዘመናዊ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በመጀመሪያው ምዕራፍ 10 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ የሚጠይቅ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ግንባታ እየተከናወነ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ 32፣ በሌሎች የክልል ከተሞች ደግሞ 8፣ በድምሩ 40 የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለአገልግሎት ለማብቃት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review