AMN- መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
የመጪውን የትንሳኤ በዓል ምክንያት በማድረግ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ግዙፍ የገበያ ማዕከል የሸማቹን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቦታው ተገኝቶ አረጋግጧል።።
በማዕከሉ ግብይት ሲፈጽሙ ኤ ኤምኤን የነጋጋራቸው ሸማቾች እንደገለጹት፤ የአቅርቦት እጥረት የሌለ ከመሆኑም በላይ ዋጋውም ከውጭ ገበያ አንጻር እጅግ የተሻለ ነው።
ለምሳሌ ቲማቲም በ35 ብር እና ሽንኩርት በ65 ብር እየቀረበ መሆኑን የጠቀሱት ሸማቾች፣ በአንድ ቦታ ሁሉንም ምርት ማግኘት መቻላቸውን በአዎንታዊነት አንስተዋል።
ሆኖም አንዳንድ ነጋዴዎች ምርቱን ከተለጠፈው ዋጋ በላይ እንደሚሸጡ ጠቁመው፣ መንግስት የቁጥጥር ስራውን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።
ነጋዴዎች በበኩላቸው ምርቶችን በቀጥታ ከአምራቾች በማምጣት ለሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ነጋዴ ትግስት አለሙ እንደተናገሩት፣ በውጭ ገበያ እስከ 1 ሺህ800 ብር የሚሸጠው ቅቤ በማዕከሉ በ980 ብር እየቀረበ ሲሆን፤ እንቁላልም በ16 ብር ለሸማቹ እየቀረበ ይገኛል። በተጨማሪም ቡና፣ ቅመማ ቅመሞች እና በርበሬ ይዘው መቅረባቸውን ነጋዴዎች አረጋግጠዋል።

የገበያ ማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ምህረቱ ቀና፣ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ የገበያ ማረጋጋት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። “ምርቶቻችን ከውጭ ገበያ ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ አላቸው” ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ከተለጠፈው ዋጋ በላይ በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ከንግድ ቢሮ ተቆጣጣሪዎች ጋር በመሆን ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኑሮ ውድነቱን ጫና ለመቀነስ እና ገበያውን ለማረጋጋት የቀረጻቸው ዘርፈ ብዙ ስልቶች አካል የሆነው ይህ የማረጋጋት ስራ፣ ሸማቹ በዓሉን ያለ ስጋት እንዲያሳልፍ ትልቅ እገዛ እያደረገ መሆኑ ተመልክቷል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ