AMN- መጋቢት 29/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መጪውን የፋሲካ በዓል ያለምንም የገበያ ችግር እንዲያሳልፉ፣ ሰፊ የገበያ ማመቻቸትና የቁጥጥር ሥራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ የበአል ግብይቱን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል በአቅርቦት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ስልታዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል። ለዚህም በመዲናዋ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የባዛር ማዕከላት እንዲከፈቱ መደረጉን ጠቁመዋል።
የሰብል ምርቶች ቀድመው ወደ ከተማዋ የገበያ ማዕከላት እንዲገቡ መደረጉን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፤ ሌሎች ለበዓል የሚሆኑ ግብዓቶችም ከተለያዩ ክልሎች ጋር በመቀናጀት እንዲቀርቡ መደረጉን ተናግረዋል።
እነዚህ የገበያ አማራጮች በባዛሮች፣ በማህበራትና በግሉ ዘርፍ አማካኝነት እንዲቀርቡ ምቹ መደላድል ተፈጥሯል። ይህም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በዓሉን ያለምንም የኢኮኖሚ ጫና እንዲያሳልፉ ታስቦ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
ከሥጋ አቅርቦት ጋር ተያይዞም በመዲናዋ ከሚገኙ ከ260 በላይ የማኅበራት ሉካንዳዎች ጋር በመቀናጀት፣ የእርድ አቅርቦትን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን አቶ ጃንጥራር አንስተዋል።
ለበዓሉ የተሳካ የገበያ ማመቻቸት ሥራ ከመከናወኑ ባሻገር፤ ሕገ-ወጥ የዋጋ ጭማሪንና የገበያ መዛባትን ለመከላከል የቁጥጥርና የክትትል ሥራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።
በሄኖክ ዘነበ