ለትንሳዔ በዓል የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪው መቅረቡን አረጋግጠናል – አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር

You are currently viewing ለትንሳዔ በዓል የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪው መቅረቡን አረጋግጠናል – አፈ ጉባኤ ቡዜና አልከድር
  • Post category:በዓል

AMN – ሚያዝያ 3/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ የቀረቡ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች አቅርቦት በበቂ ሁኔታና በተመጣጣኝ ዋጋ ለነዋሪው እየቀረቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር አስታወቁ ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር የተመሩ የልዑካን ቡድን በቂርቆስ፣ በአቃቂ ቃሊቲ እና በየካ ክፍለ ከተሞች በመዘዋወር የገበያ ሁኔታውን የቃኙ ሲሆን ፤ የከተማ አስተዳደሩ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የወሰዳቸው እርምጃዎች ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በምልከታችን ዶሮ በውጭ ገበያ እስከ 3000 ብር ቢጠራም፣ መንግስት ባመቻቸው ቦታ ግን እስከ 800 ብር እየተሸጠ መሆኑን አይተናል፡፡ ይህሞ አስተዳደሩ ገበያው እንዲረጋጋ ያቀደው እቅድ መሳካቱን ያሳያል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የንግድ፣ ኢንደስትሪና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋትዌች ዋር እንደገለጹት፣ ከተማ አስተዳደሩ ከክልሎች ጋር ባደረገው የንግድ ትስስር ምክንያት የምርት እጥረት እንዳይከሰት ተደርጓል።

ምክር ቤቱም የግብይት ሂደቱ በስኬት እንዲከናወን ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ሲያደርግ መቆየቱን አረጋግጠዋል።

ኤ ኤም ኤን በገበያ ቦታዎቹ ተገኝቶ ያነጋገራቸው ሸማቾች እና አምራቾች በበኩላቸው የዋጋ ልዩነቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው መደበኛ ገበያ ላይ እስከ 120 ብር ይሸጥ የነበረ ምርት በሰንበት ገበያዎች በግማሽ ዋጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የምርት አቅራቢዎችም ምርቶችን በቀጥታ ከክልሎች በማምጣት ለነዋሪው እያቀቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ የገበያ መረጋጋት አስተዳደሩ በአንድ በኩል አቅም ለሌላቸው ማዕድ የማጋራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ አቅም ላለው ነዋሪ ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ያስቻለ መሆኑ ተመልክቷል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review