ኢትዮጵያ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና በሴቶች ተጠቃሚነት ረገድ ጠንካራ አመራር ማሳየቷ ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነትና በሴቶች ተጠቃሚነት ረገድ ጠንካራ አመራር ማሳየቷ ተገለጸ

AMN – ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም

​13ኛው የምስራቅና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የሥርዓተ-ፆታ እና የሴቶች ጉዳይ ቴክኒካዊ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል። በስብሰባው ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

​የኮሜሳ ሴክሬታሪያት የፕሮግራሞች ረዳት ዋና ፀሐፊ አምባሳደር መሀመድ ካዳ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍም ሆነ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጠንካራ አመራር እያሳየች መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ጥረቷ ኢትዮጵያ በምሳሌነት የምትጠቀስ ሀገር መሆኗን አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል።

​የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለዘላቂ ልማት ብቻ ሳይሆን ለቀጠናዊ ውህደትም ወሳኝ መሆኑን አምባሳደር መሀመድ አስረድተዋል።

ኮሜሳ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የሥርዓተ-ፆታ ምላሽ ሰጪ ፖሊሲዎችን፣ የሕግ ማዕቀፎችን እና ​ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችን ለመደገፍ ጽኑ ቁርጠኝነት እንዳለውም አረጋግጠዋል።

​የኢፌድሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂክማ ኬይረዲን በበኩላቸው፤ አካታች እና ቀጣይነት ያለው ልማት ያለ ሴቶች ሙሉ እና እኩል ተሳትፎ ሊሳካ እንደማይችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን እና የሴቶች ተጠቃሚነትን በተመለከተ የገባቻቸውን ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎች ይበልጥ ለማጣጣም፣ በአሁኑ ወቅት የተሻሻለ ፖሊሲ በማዘጋጀት ላይ መሆኗን ይፋ አድርገዋል።

​ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለውም በኮሜሳ ስር የሚገኝ ጠንካራ እና የተቀናጀ ገበያ ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቁመው፤ ድንበር ተሻጋሪ ንግድን በማሳደግ፣ መሰናክሎችን በመቀነስ እና አካታች የኢኮኖሚ ዕድሎችን በመፍጠር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ከድህነት ማውጣት ይቻላል ብለዋል።

​ሴቶች እና ሕፃናት የልማት አጀንዳዎች እምብርት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም አባል ሀገራት በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ይህ 13ኛው የቴክኒካዊ ኮሚቴ ስብሰባ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል።

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review