ኢትዮጵያ የባህር በር አስፈላጊነት ላይ የያዘችው አቋም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የባህር በር አስፈላጊነት ላይ የያዘችው አቋም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

AMN- ሚያዚያ 7/2018 ዓ.ም

ዓለም አቀፍ የንግድና የሎጂስቲክስ መስመሮች ባልተጠበቀ አለመረጋጋት ውስጥ በወደቁበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት የባህር በር አስፈላጊነት ላይ የያዘችው የአርቆ አሳቢነት አቋም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።

ሀገራዊ ጥቅምን ለማስከበር ከባህር በር መራቅ የማይታሰብ መሆኑንም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አሁን ዓለም ባለችበት ተለዋዋጭ ሁኔታ መከተል የሚገቡ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን በዝርዝር አብራርተዋል።

የዘመኑን ቴክኖሎጂና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ማወቅ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀየረ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት የንግድ ውጥረቶችን፣ ድንገተኛ ወረርሽኞችን እና ጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክሮችን ጠቅሰዋል።

በዓለም ላይ በአየር፣ በየብስና በባህር የሚደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ አለመረጋጋት እየታየ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት ለኃያላን መንግስታት የባህር ላይ እንቅስቃሴ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችልና በዚህም ምክንያት 130 ሚሊዮን ሕዝብ ስጋት ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል ገልጸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህንን የመንግስት የአርቆ አሳቢነት አቋም አሁን ላይ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ የሀገርን ጥቅም ማዕከል ያደረገ ተጨባጭና በተግባር ላይ ያተኮረ “ፕራግማቲክ” የሆነ አካሄድ መከተል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሀገራት እና ኩባንያዎች በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆኑ “ፕላስ ዋን” (Plus One) የተሰኘ ስትራቴጂን መከተል እንደሚገባ አስረድተዋል።

እንዲሁም ኢንቨስትመንቶቻቸውን ታማኝና ቅርብ በሆኑ አገራት እያሰፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የዓለም የስነ-ህዝብ ስብጥር ወይንም ዴሞግራፊ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀየረ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይ በበለጸጉት አገራት የአምራችና የሸማች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ለምርትና ለፍጆታ አደጋ እንዳለው ጠቁመዋል።

በአንጻሩ አፍሪካ ያላት ሰፊ የወጣት ኃይልና ገበያ ኢንቨስትመንት ወደ አህጉሪቱ ለመሳብ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ ዓለም ወደ “አረንጎዴ ኢኮኖሚ” እያመራች መሆኑንና ኢትዮጵያም እነዚህን አዝማሚያዎች ተረድታ መጓዝ እንዳለባት አሳስበዋል።

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review