AMN- ሚያዝያ 9/2018 ዓ.ም
ዳሊላ ሙሐመድ እ.አ.አ የካቲት 7 ቀን 1990 በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ ኩዊንስ ውስጥ ተወለደች።
ያደገችው በሃይማኖታዊ እና በማህበራዊ አገልግሎት በሚተጋ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን፣ አባቷ አስኪያ ሙሐመድ የእስልምና ሃይማኖት መምህር ሲሆኑ፣ እናቷ ናዲራ ደግሞ የሕፃናት ጥበቃ ባለሙያ ነበሩ።
የዳሊላ የስፖርት ተሰጥኦ የታየው ገና የአራት ዓመት ልጅ ሳለች ነበር።
በአካባቢው የሚገኝ አንድ አሰልጣኝ በመንገድ ላይ ቁሶችን ስትዘል ካያት በኋላ፣ እናቷ በኒው ዮርክ ናቫስ ትራክ ክለብ ውስጥ እንድታስመዘግባት መከራት።
ይህም ለወደፊት ስኬቷ የመጀመሪያው እርምጃ ሆነ።
በቤንጃሚን ኤን ካርዶዞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለችም በስፖርቱ ዓለም ስሟ መታወቅ መጀመሩን ግለ ታሪኳ ያስረዳል።
እ.ኤ.አ. በ2007 በዓለም ታዳጊዎች ሻምፒዮና በ400 ሜትር መሰናክል ወርቅ በማግኘቷ ትልቅ ተስፋ የተጣለባት አትሌት ሆነች።

ከዚያም በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር ትምህርቷን እየተከታተለች በዩኒቨርሲቲው የስፖርት ቡድን ውስጥ ትልቅ ስኬቶችን አስመዝግባለች።
የዳሊላ የሩጫ ሕይወት በታላላቅ ድሎች የተሞላ ሲሆን ፣ ይህም እ.አ.አ 2016 ሪዮ ኦሊምፒክ በ400 ሜትር መሰናክል ለአሜሪካ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በማምጣት ታሪክ ሰርታለች።
እ.አ.አ በ2019 በኳታር መዲና ዶሃ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በራሷ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ52.16 ሰከንድ በማሻሻል የወርቅ ሜዳሊያ አሸንፋለች።
በታሪክ እጅግ ፈጣን በተባለው የ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድር የራሷን ክብረወሰን ማሻሻል የቻለች ቢሆንም ፣ ያሳካችው ግን የብር ሜዳሊያ ነበር።
በተጨማሪም በ400 ሜትር የቡድን ዱላ ቅብብል ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች።
በአዲስ አበባ ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የአንድ ቀን የሩጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ትገኛለች፡፡
በታምራት ቢሻው