ኢትዮጵያ በመረጃ ሉዓላዊነትና በስታቲስቲክስ ልማት አዲስ ስኬት ማስመዝገቧ ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ በመረጃ ሉዓላዊነትና በስታቲስቲክስ ልማት አዲስ ስኬት ማስመዝገቧ ተገለጸ

AMN – ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የመረጃ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ትንበያዎችን በራሷ አቅም ለማከናወን የሚያስችሏትን ስኬታማ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወኗን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የበጀት ዓመቱን ሶስተኛ የመንግሥት የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ነው።

ባለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አንዱ አካል መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ ይህም ቀደም ሲል በዘርፉ የነበረውን የመረጃ ክፍተት ከመሙላት ባለፈ ኢትዮጵያ የራሷን የኢኮኖሚ ትንተና ሞዴሎች እንድታለማ ማስቻሉን አብራርተዋል።

ሪፎርሙ የውጭ አካላት በመረጃ ትንተና ላይ የነበራቸውን ጣልቃ ገብነት በማስቀረት የሀገሪቱን የመረጃ ታማኝነትና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑም በሪፖርቱ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከናወነው የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ከ2.6 ሚሊዮን በላይ የንግድ ድርጅቶች መኖራቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።

በተጨማሪም ከ23 ዓመታት በኋላ የተካሄደው አጠቃላይ የግብርና ቆጠራ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መሆኑን ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በተለይም ዲ-ሳት የተሰኘውን የሪሞት ሴንሲንግ ሞዴል በመጠቀም፣ በአካል መድረስ በማይቻልባቸው አካባቢዎች የሰብል ምርትን በቴክኖሎጂ መተንበይ መቻሉን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የስታቲስቲክስ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ለመውሰድና ሥልጠና ለማግኘት ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙም ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው አመላክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የተቀናጀ የቤተሰብ ሰርቬይ፣ የስነ-ሕዝብና የጤና ጥናት እንዲሁም የሥራ ዕድል ፈጠራን የተመለከቱ ጥናቶች ውጤት እየተጠናቀቀ መሆኑንና ይህም ለመጪው ሀገራዊ የልማት ዕቅዶች እንደ ዋነኛ ግብዓት እንደሚያገለግል ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review