AMN- ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም
ዛሬ ሚያዝያ 15 በፈረንጆቹ (April 23) በመላው ዓለም የመጽሐፍ እና የደራሲያን መብት ቀን ሆኖ ይከበራል።
መጽሐፍ ከጊዜና ከቦታ ገደብ ተሻግረን የሰዎችን ጥበብ፣ እውቀትና ልምድ የምንቀስምበት ታላቅ ድልድይ ነው።
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ጊዜያችን በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ገፆች የሚወሰድ መሆኑ የታወቀ ነው።
ይህ የዲጂታል ሱስ ትኩረታችንን በመበታተን እና በሥነ-ልቦናችን ላይ ጫና በማሳደር ረገድ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት መጽሐፍን ማንበብ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ቁልፍ መሳሪያ ነው::
የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ይዘቶች አጫጭር እና ፈጣን በመሆናቸው የአዕምሯችንን ለረጅም ጊዜ የማተኮር ብቃት ያዳክሙታል።
መጽሐፍ ማንበብ ግን አዕምሮ በአንድ ሃሳብ ላይ ረጋ ብሎ እንዲቆይና በጥልቀት እንዲያስብ ያሰለጥነዋል።
በሀገረ እንግሊዝ በሚገኘው ሱሴክስ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በቀን ለ6 ደቂቃ ብቻ ማንበብ የጭንቀት መጠንን በ68 በመቶ ይቀንሳል።
ይህ ከሙዚቃ ማዳመጥ ወይም የእግር ጉዞ ከማድረግ በበለጠ አዕምሮን የማረጋጋት አቅም አለው።
ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን “ስለ ሁሉም ነገር ጥቂት” እንድናውቅ ሲያደርገን፣ መጽሐፍት ግን “ስለ አንዱ ነገር በጥልቀት” እንድንረዳ ያስችሉናል።
ታላቁ የሮማ ንጉሰ ነገስት ማርከስ አሌሊዮንስን በአንባቢነት ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፣ ንጉሰ ነገስቱ በጦርነትና በወረርሽኝ መካከል ሆነው እንኳን ማንበብና መጻፍን እንዳልተዉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የእሳቸው “ሜዲቴሽን” የተሰኘው መጽሐፍ ዛሬም ድረስ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ መሪዎችና ስኬታማ ሰዎች የጥንካሬ ምንጭ ነው።
“መጽሐፍት ለነፍስ ምግብ ናቸው” እንደሚባለው፣ ንባብ በዙሪያችን ላለው ፈታኝ ዓለም የምንገነባው ጠንካራ የአዕምሮ ጋሻ ነው።
ይህንን ቀን ስናከብር ስልካችንን ለጥቂት ደቂቃዎች አሳርፈን አንድ መጽሐፍ በእጃችን ይዘን ይሁን።
መጽሐፍ ማንበብ አዲስ ዓለምን ማየት፣ ከአዳዲስ ሰዎች ጋር መተዋወቅና ራስን ማግኘት ነው።
እስከ አሁን ካነበባችኋቸው መጽሐፍት ሕይወታችሁ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣው የትኛው መፅሐፍ ነው?
በያለው ጌታነህ