የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሱን ስለማሳወቅ

You are currently viewing የትራንስፖርት አገልግሎት ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለሱን ስለማሳወቅ

AMN ሚያዝያ 21/2018 ዓ.ም

በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው ግጭት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሮ፣ የነዳጅ ዋጋ ግሽበትና በአቅርቦት ላይ መስተጓጎል እንዲፈጠር አድርጓል።

ይህም ሁኔታ በኢትዮጵያ የናፍጣ ዕለታዊ አቅርቦትን ከ9 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4.5 ሚሊዮን ሊትር እንዲቀንስ አድርጎ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚታወቁ መስተጓጎሎችን አስከትሎ ነበር።

መንግሥት ይህንን ችግር በፍጥነት ለመቆጣጠር የታሪፍ ማሻሻያ፣ የአቅርቦት አደረጃጀት ማሻሻል እና የሎጂስቲክስ ቅንጅት ማጠናከር ጨምሮ በርካታ አስቸኳይ እና ዘላቂ እርምጃዎችን ወስዷል።

ይህም የውጭ ጫናዎች ቢኖሩም የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በመጠበቅ እና የህዝብ አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ በማድረግ በኩል መንግሥት የሕዝብ ጥቅምን በማስቀደም የሚከተለውን የፖሊሲ አቅጣጫ የሚያሳይ ነዉ ።

ዛሬ ሚያዚያ 21/2018 ዓ.ም የገንዘብ ሚኒስቴር በይፋ እንዳሳወቀው የነዳጅ አቅርቦት ወደ መደበኛ ሁኔታው ተመልሷል። ይህ ሁኔታ በትራንስፖርት ዘርፍ የተፈጠሩ መስተጓጎሎች በፍጥነት እንዲፈቱ ያስችላል።

በመሆኑም ከዛሬ ጀምሮ ቀደም ሲል በነዳጅ እጥረት ምክንያት የተፈጠሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሎች ሙሉ በሙሉ እንዲቀረፉ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ክልሎች የምትገኙ ሁሉም የዘርፉ አመራሮች እና ተዋናዮች ታሪፍ በተወሰነዉ መሰረት ብቻ እንዲቀጥል በጥብቅ እንድትከታተሉ እና ትግበራዉንም በጋራ ግብረሀይል እንድታረጋግጡ እናሳስባለን፡፡

መንግሥት የህዝብ ኑሮ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ቀጣይነትን መጠበቅ እና የትራንስፖርት አገልግሎት በዘላቂ መልኩ እንዲጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት ይቀጥላል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review