AMN – ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ተገንብተው፣ እድሳት እና ማስፋፊያ ተደርጎላቸው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ጤና ጣቢያዎች ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለህብረተሰቡ እየሰጡ ነው፡፡
በከተማዋ የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ወራት በ4 ቢሊየን ብር ወጪ አዲስ የተገነቡ፣ ማስፋፊያና ዕድሳት የተደረገላቸው 22 ጤና ጣቢያዎች መመረቃቸው የሚታወስ ሲሆን ፣ በጤና ተቋማቱ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠባቸው ከሚገኙት መካከል የልደታ ጤና ጣቢያ እና አስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያ ተገልጋዮች በጤና ተቋማቱ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ለኤ ኤም ኤን ተናግረዋል፡፡

በልደታ ጤና ጣቢያ ሲገለገሉ ያገኘናቸው ፍቃዱ ተስፋዬ ፣ ከዚህ በፊት ውስን አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበር ገልጸው አሁን ላይ እየታከሙበት ባለው ጤና ጣቢያ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት በአጭር ጊዜ እያገኘን ነው ብለዋል፡፡
በአስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያ ስትታከም ያገኘናት ማህሌት ተስፋዬ በበኩሏ፣ ከዚህ ቀደም በአቅራቢያዋ ጤና ጣቢያ ባለመኖሩ ህክምና ለማግኘት ወደሌላ አካባቢ መሄድ ይጠበቅባት እንደነበር አስታውሳለች፡፡ አሁን ላይ ግን በቅርበት ህክምና ማግኘት በመቻሏ ደስተኛ መሆኗንም አስረድታለች፡፡
የአስኮ አዲስ ሰፈር ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ዩሱፍ ቱግባር ፣ ጤና ጣቢያው ለአዋቂዎችና ለህጻናት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጥርስ ህክምና አገልግሎትም በጤና ጣቢያው እየተሰጠ እንደሚገኝ በመጥቀስ በተገልጋዮች ዘንድ የነበረውን እንግልት እና ወጪ እያስቀረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በጤና ጣቢያው ለአካባቢው እና በአጎራባች ላሉ ታካሚዎች በወቅቱ ዘመናዊ ህክምና እና የጤና ምክር አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በጤና ጣቢያው አገልግሎት ሲሰጡ ያገኘናቸው የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው ፣ አሁን ላይ ለተገልጋይ ብቻ ሳይሆን ለባለሙያውም ምቹ ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ።
በልደታ ጤና ጣቢያ የተቀናጀ ድንገተኛ ቀዶ ጥገና ማህፀን ጽንስ ስፔሻሊስት ባለሙያ ዶክተር እርቁ ካሳ ፣ አሁን ላይ በጤና ጣቢያው የላቀ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደራጀ የማዋለጃ ክፍል እና ሌሎች ከቀዶ ጥገና ጋር በተያያዘ ጥራት ያለው ህክምና ለመስጠት የሚያግዙ መሳሪያዎች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የልደታ ጤና ጣቢያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አረፋት ጠሃ በበኩላቸው፤ ጤና ጣቢያው ከተመረቀ በኋላ ለህብረተሰቡ ዘመኑን ያማከለ የጤና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በየሻምበል ምህረት