ፒያሳ – ከትላንት ትዝታ ወደ ነገው ዘመናዊነት

You are currently viewing ፒያሳ – ከትላንት ትዝታ ወደ ነገው ዘመናዊነት

ANM- ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የ150 ዓመታት ታሪኳን ወደ ኋላ እያየች ፣ የነገውን ብልጽግና ደግሞ በኮሪደር ፤ ወንዝ ዳርቻ እና መሰል የልማት ስራዎች እያመላከተች ትገኛለች።

የከተማዋ እምብርት የሆነችውና በታሪክ ማህደር ውስጥ ደማቅ ስም ያላት ፒያሳ ፣ ዛሬ የዚህ ትልቅ ለውጥ ማሳያ ሆና አዲስ መልክ እየያዘች ነው።

የአራዳ ልጅነትና የፒያሳ ስያሜ

አዲስ አበባ ስትቆረቆር ሶስት ማዕከላትን ግቢን፣ አራዳንና የቤተክርስቲያን ቅጥርን መሰረት አድርጋ እንደነበር ይታወሳል።

የዛሬዋ ፒያሳ በወቅቱ “አራዳ” ተብላ የንግድና የገበያ ማዕከል ነበረች።

በ1928ቱ የጣልያን ወረራ ወቅት ግን ስሟ ወደ ፒያሳ ተቀይሮ የመዝናኛ ስፍራ ሆነች።

ይሁን እንጂ ከሚያማምሩት የፊት ለፊት ገጽታዎቿ በስተጀርባ፣ ለዘመናት የቆዩና ለኑሮ የማይመቹ፣ የተጎሳቆሉ ሰፈሮች ተሸሽገው ቆይተዋል።

ይህን የታሪክና የኑሮ ደረጃ ልዩነት ለማጥበብ የኮሪደር ልማቱ ፒያሳን በአምስት ዋና ዋና ዘርፎች ዳግም እየቀረጻት ይገኛል።

የለውጡ አምስት ምሰሶዎች

ክብር ለነዋሪዎቿ፦ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለነበሩ ዜጎች የተሻለና ዘመናዊ መኖሪያን በማቅረብ፣ የሰው ልጅ በክብር የመኖር መብቱን በተግባር አረጋግጧል።

የግል ባለይዞታዎችም ተገቢውን ካሳና ምትክ ቦታ በማግኘት የልማቱ ተሳታፊ ሆነዋል።

መሰረተ ልማት እንደ አዲስ፦

ፒያሳ ከነበረባት መጨናነቅ ወጥታ በአራት አዳዲስ ሰፊ ጎዳናዎች ውበቷ እጅጉን ደምቋል።

የወንዝ ዳርቻዎቿ ወደ ማራኪ መናፈሻነት ሲቀየሩ፣ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችና የትራንስፖርት ተርሚናሎችም የከተማዋን ስልጣኔ አጉልተውታል።

ቅርስን ለትውልድ ማሻገር፦

ልማቱ ከተማን ብቻ ሳይሆን ታሪክን እና ቅርስን ጭምር የሚያለማና የሚያስተዋዉቅ ለመሆኑ ፒያሳ ምስክር ናት።

የ126 ዓመቱ የቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ቤት እና የአሮጌው ማዘጋጃ ቤት ህንጻዎች በባለሙያ ታድሰው ለቱሪስት መዳረሻነት በቅተዋል።

የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል፦

የፒያሳ የንግድ መንፈስ ይበልጥ ዘምኗል፤ በዘመናዊ የንግድ ህንጻዎች ታጅቦ ለገበያ ምቹና ማራኪ ሆኖ ቀጥሏል።

የከተማዋ አዲስ ምልክት

ታላቁ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፒያሳን የኩራትና የክብር መዳረሻ አድርጓታል።

ዛሬ ፒያሳ የሀገር መሪዎች የአበባ ጉንጉን የሚያስቀምጡባት ፣ ጎብኚዎች የሚሰበሰቡባት፤ አህጉርና አለም አቀፍ ኩነቶች የሚካሄዱባት የአዲስ አበባ አዲሷ ፈርጥ ሆናለች።

ፒያሳ ጥንታዊ ወርቅ ቤቶቿን ፣ ሲኒማ ቤቶቿንና ታሪካዊ ጠረኗን ይዛ ፣ በዘመናዊ መሰረተ ልማት ተውባ ዳግም ተወልዳለች።

ይህ የኮሪደር ልማት ውጤት አዲስ አበባን እንደ ስሟ “አበባ” በማድረግ፣ ነዋሪዎቿን ከጎጆ ወደ ዘመናዊ ህይወት ያሸጋገረ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review