ቃል በተግባር፣ ኢትዮጵያ እያከናወነች ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing ቃል በተግባር፣ ኢትዮጵያ እያከናወነች ነው – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN ግንቦት 3/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች የጀመረቻቸው ግዙፍ ተግባራት የትውልድ ተስፋ ከመሆን ባለፈ፣ በተጨባጭ ስኬቶች የታጀቡና ቃል በተግባር የተፈጸመባቸው ድሎች ሆነዋል።

በግብርናው ዘርፍ፣ በተለይም በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የታየው ዐቢይ ለውጥ ሀገሪቱን ከውጪ የዕርዳታ ስንዴ ጥገኝነት አላቆ ራስን ወደ መቻል ከፍ አድርጓታል። ምርቱን ለውጭ ገበያ ማቅረብ (ኤክስፖርት) መጀመሯም፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ትግል ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

በኢንዱስትሪው መስክ የውጭ ምንዛሬ ፍሰትን ለመታደግ የተወጠነው “የተኪ ምርቶች ንቅናቄ”፣ የኢንዱስትሪ ግብአቶችንና የፍጆታ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል። ይህም ሀገራዊ ምርታማነትን በማነቃቃት የኢኮኖሚውን መዋቅር እያጠናከረ ነው።

የከተሞችን ገጽታ ለማሻሻልና ለዜጎች ክብር ያለው ሕይወት ለመስጠት የተጀመረው የኮሪደር ልማት፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የክልል ከተሞችን የኮንፈረንስ ቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ፣ ምቹ የመንቀሳቀሻ መንገዶችንና ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶችን እውን በማድረግ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ላይ አዲስ ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል።

የኢትዮጵያዊያን የጋራ ትብብር ማሳያ በሆነው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ኢትዮጵያ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በሚደረገው አለም አቀፍ ጥረት ቀዳሚ ከሆኑ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ያደረገ የማይደበዝዝ አሻራ ማኖር ትችሏል።

ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማደስ ፣ አዳዲስ መዳረሻዎችን በመገንባት እና የንጹህ ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶችን በማስፋፋት ሀብቶች እንዲለዩ እንዲገለጡ እና የኢኮኖሚ መሰረት እንዲሆኑ የተሰራው ወሳኝ ሥራ ፍሬው የሚታይበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ይገኛል፡፡

እነዚህ ስኬቶች የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ቁርጠኝነት ውጤቶች ናቸው። ኢትዮጵያ በትክክለኛ የልማትና የዕድገት ጎዳና ላይ መሆኗን የሚያረጋግጡ ከመሆናቸውም በላይ፣ በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚመጣበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን ያሳያሉ።

የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review