AMN – ግንቦት 4/2018 ዓ.ም
ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረውና በጠንካራ የታሪክ መሠረት ላይ የቆመው የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ዛሬም በአዲስ ጉልበትና በላቀ ትብብር ቀጥሏል።
ፈረንሳይ እ.ኤ.አ. በ1897 በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በመክፈት የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሀገር በመሆን ታሪካዊ አሻራዋን ካሳረፈችበት ጊዜ ጀምሮ፣ በምድር ባቡር፣ በትምህርት እና በጤና ዘርፎች የኢትዮጵያ የቅርብ አጋር ሆና ዘልቃለች።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ለመጠገንና ለመንከባከብ የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ (AFD) ከፍተኛ የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ይህ ታላቅ ፕሮጀክት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ለታሪክና ለቅርስ ጥበቃ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
በተጨማሪም፣ ታሪካዊው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተገቢው ጥገና ተደርጎለት ለጎብኚዎች ክፍት እንዲሆን የሚደረገው ድጋፍ ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ ፋይዳ አለው።
የሁለቱ ሀገራት ትብብር በአርኪኦሎጂያዊ ምርምር ዘርፍም የጎላ ድርሻ አለው። በአክሱም እና በላሊበላ አካባቢዎች ለበርካታ አስርት ዓመታት በጋራ የተከናወኑ ሳይንሳዊ ጥናቶች ለሀገሪቱ የታሪክ ሀብት መበልጸግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ከዚህም ባለፈ፣ ከ1940ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ የተመሠረተው “አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴዝ” የኢትዮጵያን የጥበብና የሙዚቃ ዘርፍ በማሳደግ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል እንደ ጠንካራ የባህል ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ይህ ታሪካዊ ወዳጅነት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግ ወደ ተለያዩ ዘመናዊ ዘርፎች ተሸጋግሯል።
በተለይም በታዳሽ ኃይል ልማት፣ በግብርና ማዘመን እና በሰላም ማስከበር ተግባራት ላይ ትብብሩ ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የቱሪዝም አቅም ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የፈረንሳይ መንግሥት የሚያሳየው ቁርጠኝነት፣ የሁለቱን ሀገራት የወደፊት የጋራ ትብብር ይበልጥ የሚያጠናክር ነው።
በበረከት ጌታቸው